አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በአንድ ሀገር ጉዳይ ላይ አቋም ከወሰደ፣ የመንግስት አቋም አድርገን ነው የምንወስደው- ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኡጋንዳ በህወሃት ላይ ያላትን አቋም ለማወቅ የኡጋንዳን አምባሳደር ጠርተው ማነጋገራቸውን ገልጸል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በትናንትናው እለት ኡጋንዳ ለህወሓት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን እና ይህን የኢትዮጵያ መንግስት እንዴት እያየው ነው በሚል ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ነው፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኡጋንዳ ካምፓላ ያሉት የኢትዮጵያ አምባሳደርም ይፋዊ መልእክት ለኡጋንዳ መንግስት ማቅረባቸውን እና ማብራሪያ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የወታደራዊ ኦፊሰሮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ከኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር መወያየቷን የገለጹት ሚኒስትሩ ጉዳዮ “በቀላሉ የሚያይ እና የሚተው አይደለም” ብለዋል፡፡
ጉዳዩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዝርዝር መገምገሙን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“እንዳንዴ የሚሉት ምንድነው፣ ይሄ በራሳቸው የሚኖሩና እና ራሳቸው የሚጠየቁበት ነው፤ እኛ ይሄን አንደግፍም ይላሉ፡፡”
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት አንድ የኡጋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣን በአንድ ሀገር ጉዳይ ላይ አቋም ከወሰደ፣ የመንግስት አቋም አድርገን ነው የምንወስደው ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
ሚኒስትሩ ኡጋንዳ ግልጽ አቋሟን እንድታሳውቀን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳንንም ህወሓትን ትደግፋለች በሚል ከሷል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መሬት መያዟን እና የህወሓት ሃይል መነሻ በመሆን ችግር እየፈጠረች መሆኑን የገለጹት ሚኒስተሩ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አሻክሮታል ብለዋል፡፡
ሚኒስተሩ በሱዳን የተወሰደው ኢትዮጵያ ግዛት በየትኛውም መመዘኛ እንደሚመለስም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን ሰላምዊ መፍትሄ አላገኘውም፤አልተቋጨም፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው ጦርነት በሺዎች እንዲሞቱ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እና ህይወታቸው እንዲመሳቀል አድጓል፡፡