የኢትዮጵያ መንግስት በህወሓት ጉዳይ የኡጋንዳን አምባሳደር ጠርቶ ማወያየቱን መግለጹ ይታወሳል
በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሃት በኡጋንዳ ታጣቂዎቹን እያሰለጠነ እንደሆነ እነ ድጋፍ እየተደረገለት ነው የሚሉ ዘገባዎች ከሰሞኑ በስፋት ሲሰራጩ ቆይተዋል።
ቢቢሲ የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ዜናው ሆን ተብሎ የተፈበረከ ነው ተብሏል።
ከፌደራል መንግስት ጋር ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ያለው ህወሃት በኡጋንዳ ጦር ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ መሰቱን ኒውዝላንድ ያደረገው እና ስኩፕ የተሰኘው የበይነ መረብ ሚዲያ ዘግቦ ነበር።
ይሔንን ተከትሎም በበርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ኡጋንዳ ጉዳዩ ሀሰት እንደሆነ አስተባብላለች።
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ፌሊክስ ኩላጊይ ለቢቢሲ እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ ህወሃትን ታሰለጥናላችሁ በሚል የቀረበው ክስ ሀሰት ነው ብለዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የወጣው ዘገባ ህወሃት በማዕከላዊ ኡጋንዳ ማሳካ ግዛት ከአራት ሺህ በላይ ለሆኑ ታጣቂዎች ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ይጠቅሳል።
እንዲሁም ይህ የህወሃት ታጣቂዎች ስልጠና በግብጽ እና አሜሪካ እንደሚደገፍም በኡጋንዳ አራት ቦታዎች ላይ በመሰጠት ላይ መሆኑንም ያወሳል።
ይሄ የህወሃት ታጣቂዎች ስልጠናው በኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ልጅ እና በሀገሪቱ የምድር ጦር አዛዥ ጀነራል ማሁዚ ኬኒሩጋባ እንደሚታገዝም ዘገባው ያትታል።
ጀነራል ሙሁዚ ከዚህ በፊት በተረጋገጠው የትዊተር ገጻቸው የህወሃት ታጣቂዎችን ወንድሞቼ በሚል መጥራታቸውን ዋቢ ያደረገው ይህ ዘገባ ህወሃትን ለመርዳታቸው እንደ አጋዥ መረጃም ተቆጥሯል።
ስለ ዚህ ዘገባ የተጠየቁት የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ከህወሃት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማተራመስ አሲረዋል መባሉን አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዚህ ቀደም ኡጋንዳ በህወሃት ላይ ያላትን አቋም ለማወቅ የኡጋንዳን አምባሳደር ጠርተው ማነጋገራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኡጋንዳ ለህወሓት ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን እና ይህን የኢትዮጵያ መንግስት እንዴት እያየው ነው በሚል ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ እንደነበረም አይዘነጋም።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኡጋንዳ ካምፓላ ያሉት የኢትዮጵያ አምባሳደርም ይፋዊ መልእክት ለኡጋንዳ መንግስት ማቅረባቸውን እና ማብራሪያ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የወታደራዊ ኦፊሰሮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ከኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር መወያየቷን የገለጹት ሚኒስትሩ ጉዳዮ “በቀላሉ የሚያይ እና የሚተው አይደለም” ብለዋል።