ዓለም ባንክ ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በመከልከሏ ብድር እንደማይሰጥ አስታውቋል
የተመሳሳይ ጸታ ጋብቻን የሚከለክል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ ብድር እና ሌሎች ድጋፎችን የተከለከለችው ኡጋንዳ ያለአለም ባንክ ድጋፍ ህይወትን ለመቀጠል እቅድ ማዘጋጀቷ ተሰምቷል።
የዓለም ባንክ ለኡጋንዳ አዲስ ብድር እንደማይሰጥ ማስታወቁን የሚታወስ ሲሆን፤ ኡጋንዳም ያለ አለም ባንክ ድጋፍ መኖር እንደምትችል ማሳወቋ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ኡጋንዳ ያለአለም ባንክ ድጋፍ ህይወትን ለመቀጠል የሚያስችል እቅዶችን መንደፏን የኡጋንዳው ሞኒተር ጋዜጣ በድረ ገጹ አስንብቧል።
በዚህም ኡጋንዳ አዳዲስ የገንዘብ ምንጮችን እያፈላለገች ነው የተባለ ሲሆን፤ ከኢነዚህም ውስጥ እንደኛው በአፍሪካ ውስጥ ተጽእኖዋ እያደገ ከመጣው ቻይና ጋር ተቀራሮቦ መስራት ነው ተብሏል።
ከህንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳደግንም እንደ አማራጭ ያዘችው የኡጋንዳ፤ የዩሮ ቦንዶችን ማዘጋጀት እና ለጨረታ በማቅረብ ገንዘብ ለማግኘት መወጠኗም ተነግሯል።
ሌላኛው ኡጋንዳ እንደ አማራጭ የያዘችው መፍትሄ በሀገር ውስጥ የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ማስተካከያዎችን መውሰድ ሲሆን፤ በዚህም ሀገሪቱ ለመንግስት ባለስልጣናት በውድ ብር ሊገዙ የነበሩ የመኪናዎችን ግዢዎችን መሰረዟን እና ከዚህ በኋላ አዳዲስ የመኪና ግዢ እንደማይሮም የሀገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ የሚከለክል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ በምዕራባዊያን ሀገራት ስትወገዝ ቆይታለች።
ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው ኡጋንዳ ያለ ዓለም ባንክ ብድር ማደግ ትችላለች ማለታቸው ይታወሳል።።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም " የዓለም ባንክ እምነታችንን፣ ሉዓላዊነታችንን እን ባህላችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ምዕራባዊያን "አፍሪካን ዝቅ አድርገው መመልከት እና ጫና ማሳደር ይፈልጋሉ፣ እኛ ችግራችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን እናውቃለን፣ እነሱም የእኛ ችግሮቻችን ናቸው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኡጋንዳ ከዓለም ባንክ ጋር ያለባትን ችግር ለመፍታት የሚቻል ከሆነ ውይይት ለማድረግ ትቀጥላለች ሲሉም ተናግረዋል ።
ኡጋንዳ ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከከለክል ህግን ያጸደቀች ሲሆን ፕሮዝዳንት ሙሴቪኒም ህጉ እንዲተገበር መፈረማቸው ይታወሳል።
ኣሜሪካ ኡጋንዳ ያጸደቀችውን ህግ ከመቃወም ባለፈ ማዕቀብ የጣለች ሲሆን አሁን ደግሞ የዓለም ባንክ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥሏል።