የፖል ካጋሜ ‘ያልተጠበቀ’ው የኡጋንዳ ጉብኝት ፡ በፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ የልደት በዓል ላይ መገኘታቸው እያነጋገረ ነው
ካጋሜ፤ ከሙሴቬኒ ይልቅ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሆነው የምድር ጦር አዛዡ ካይኔሩጋባ ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም የሚባል እንደሆነ ይነገራል
የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ ካይኔሩጋባ 48ኛ አመት የልደት በዓላቸውን አክብረዋል
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ከአራት ዓመታት በኋላ በኡጋንዳ ያልተለመደ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ጉብኝቱ በሁለቱም ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን ውጥረት በማርገብ፤ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ተብሎለታል፡፡
የሩዋንዳ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ እንደዘገበው ከሆነ ካጋሜ ወደ ኡጋንዳ ያቀኑት ከኡጋንዳው አቻቸው ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ለመወያየት እንዲሁም በኡጋንዳ ቁልፍ ስልጣን እንዳለው በሚነገርለት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ሙሆዚ ካይኔሩጋባ 48ኛ አመት የልደት በዓል ላይ ለመገኘት ነው፡፡
ሌ/ጄ/ል ሙሆዚ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እንዲረግብና መሪዎቹ ተቀራርበው እንዲነጋገሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወት እንደቆየ የሚታወቅ ነው፡፡
የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥና የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ ካይኔሩጋባ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ለሶስት ዓመታት ያክል ተዘግቶ የነበረውን የሁለቱ ሀገራት ድንበር እንዲከፈት በማድረግ በኩል ያበረከተው አስተዋጽኦም እንደ አብነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በዚሁ ጉብኝትም ቢሆን የሩዋንዳውን ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ካምፓላ ሲገቡ ከተቀበሏቸው የሀገሪቱ ባለስልጣናት አንዱና ዋናው እሱ መሆኑ ከሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ጋር ያለውን ግንኙነት መልካም የሚባል መሆኑ የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ካይኔሩጋባ በቅርቡ በትዊተር ገጹ ላይ ፓል ካጋሜን “አጎቴ (ፖል ካጋሜ)ን የነኩ ሁሉ ቤተሰቤን እንደነኩ አቆጥረዋለሁ ፤ ስለዚህም ቢጠነቀቁ ይሻላል” በማለት ያጋራው ጽሁፉ አነጋጋሪ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የአሁኑ ጉብኝት ኡጋንዳ፤ በሩዋንዳ መንግስት እንደ ሽብርተኛ ቡድን የሚቆጠረውንና ፖል ካጋሜን በጠብመንጃ ከስልጣን ለማስወገድ የሚንቀሳቀሰውን የሩዋንዳ ናሽናል ኮንግረስ (አር.ኤን.ሲ) መሪ የሆኑትን የቀድሞ የሩዋንዳ ኢታማዦር ሹም ካዩምባ ያምዋሳን፤ ከሀገሯ ማባረሯ ተከትሎ የተደረገ ሳይሆን አልቀረምም ተብሏል፡፡
ኡጋንዳ አማጺ ቡድኑን በማስጠጋቷ ምክንያት ሩዋንዳ ቅር ተሰኝታ ነበረ፡፡ ካጋሜ ለመጨረሻ ጊዜ ኡጋንዳን የጎበኙት እንደፈረንጆቹ መጋቢት 2018 ነው፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከ1980ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ጊዜያቶች ጥሩ የሚባል ወዳጅነት የነበራቸው ቢሆንም በኋላ ላይ አንዱ የአንዱን ተቃራኒ የሆኑት ኃይሎችን (የስለላ ሰንሰለቶች፣ አፈና እና አማፂያንን) ይደግፋል በሚል ሲወነጃጀሉ ይደመጣሉ፡፡
ሌ/ጄ/ል ሙሆዚ አባታቸውን ተክተው ኡጋንዳን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በመዘጋጀት ላይ ናቸው በሚል ሲነገር ሰንብቷል፡፡