ኤለን መስክ በ2027 የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ይሆናል ተባለ
የ53 አመቱ ቢሊየነር ሃብት በየአመቱ በ110 በመቶ እያደገ መሆኑን አዲስ ጥናት አመላክቷል
በፎርብስ እለታዊ የቢሊየነሮች ዝርዝር መስክ በ241 ቢሊየን ዶላር የአለማችን ቁጥር አንድ ሆኖ ተቀምጧል
ኤለን መስክ በ2027 የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር እንደሚሆን ተመላከተ።
“ኢንፎርማ ኮኔክት አካዳሚ” የተሰኘ ተቋም ይፋ እንዳደረገው የ53 አመቱ ቢሊየነር የሃብት እድገት ከሶስት አመት በኋላ የአለማችን ቀዳሚው ትሪሊየነር መሆን የሚያስችለው ነው።
ተቋሙ የኤለን መስክ ሃብት በየአመቱ በአማካይ በ110 በመቶ እየጨመረ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።
የ”ትሪሊዮን ዶላር ክለብ”ም በቅርቡ ባወጣው መረጃ የመስክ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ቴስላ የገበያ ዋጋ ወደ 670 ቢሊየን ዶላር ከፍ ማለቱን መግለኡን ስካይ ኒውስ አስታውሷል።
የቴስላ ዋጋ በየአመቱ በአማካይ በ173 በመቶ መጨመሩ ኩባንያው ብቻ በቀጣዩ አመት ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ዋጋ እንደሚኖረው ያመላክታል።
በፎርብስ እለታዊ የቢሊየነሮች ዝርዝር በ241 ቢሊየን ዶላር የአለማችን ቁጥር አንድ ሆኖ የተቀመጠው ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊየን ዶላር ከገዛ በኋላ የሚሰጣቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች ገቢውን ሲጎዱት ታይተዋል።
በተለይ በአይሁዳውያን ላይ የሰጠው አስተያየት ቢሊየነሩን ደረጃውን ዝቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።
በቅርቡም ከብራዚሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ ጋር የገባው ሰጣ ገባ የኤክስ (ትዊተር) ደንበኞቹን እንዳያሳጣው ስጋት ፈጥሯል።
በአንጻሩ መስክ ለ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካኖች እጩ ዶናልድ ትራምፕ ይሁንታ ሰጥቶ በቀጥታ ቃለምልልስ ማድረጉ ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ በሃብት ላይ ሃብት እንዲደርብ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
“ኢንፎርማ ኮኔክት አካዳሚ” ከኤለን መስክ ቀጥሎ የትሪሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ህንዳዊው ጓታም አዳኒ ናቸው ብሏል።
በ80 ቢሊየን ዶላር በፎርብስ የቢሊየነሮች ደረጃ 17ኛ ላይ የተቀመጡት አዳኒ ኩባንያ “አዳኒ ግሩፕ” ሃብት በአመት የ123 በመቶ እድገት እያስመዘገበ ሲሆን፥ በ2028 ባለቤቱን ወደ ትሪሊየነርነት ይለውጣል ተብሏል።
የኒቪዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀንሰን ሁዋንግ፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ቁፋሮ ቢሊየነር ያደረጋቸው ኢንዶኔዥያዊው ፕራጆጎ ፓንጌስቱም በ2028 ትሪሊየነር ይሆናሉ ተብለው ከተገመቱት መካከል ናቸው።