የኤለን መስክና የብራዚል ጠቅላይ ፍርድቤት ፍጥጫ መንስኤ ምንድን ነው?
የብራዚል ጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ ኤክስ (ትዊተር) ትዕዛዜን ካልፈጸመ በየቀኑ 19 ሺህ 736 ዶላር ይቀጣል ሲሉ አሳስበዋል
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትም መስክ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል
የአለማችን ቁጥር ሶስት ቢሊየነር ኤለን መስክ በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲቀርብ መጠየቁን ገለጸ።
መስክ በምክርቤቱ ቀርቦ ማብራሪያ እንዲሰጥ የተጠየቀው “የብራዚልን ህግ ጥሰሃል” በሚል መሆኑን በግል የኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
የብራዚልና የኤለን መስክ ፍጥጫ የጀመረው ባለፈው ቅዳሜ ነው።
የብራዚል ጠቅላይ ፍርድቤት ዳኛ አሌክሳንደር ደ ሞራይስ ኤክስ የተወሰኑ የብራዚል ፓርላማ አባላት እና የበርካታ ጋዜጠኞችን አካውንት እንዲዘጋ መጠየቃቸውም የውዝግቡ መነሻ ነው።
ዳኛ ሞራይስ “ዲጂታል ሚሊሻ” ሲሉ በገለጿቸውና ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ ባሏቸው አካላት ላይ ምርመራ መጀመራቸው ሲገለጹ ቆይተዋል።
ኤክስ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄር ቦልሶናሮ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉና በስም ያልተጠቀሱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን አካውንት እንዲዘጋ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ግን አዎንታዊ አልነበረም።
ዳኛ ሞራይስን “ሀፍረተቢስ፤ የብራዚልን ህገመንግስት የጣሱ” በማለትም ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን የሚያመላክት ጽሁፍ መስክ እሁድ እለት በኤክስ ገጹ ላይ ማስፈሩ ይታወሳል።
አሜሪካዊው ቢሊየነር ዳኛው ከሃላፊነታቸው እንዲለቁ መጠየቁን ተከትሎም የጠቅላይ ፍርድቤቱ ዳኛ ኤክስ ትዕዛዜን ካላከበረ በየቀኑ 19 ሺህ 736 ዶላር ይቀጣል ማለታቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ዳኛ ሞራይስ ከገንዘብ ቅጣቱ ባሻገር የኩባንያውን ሰራተኞች በቁጥጥር ስር እንደሚያውሉና ኤክስ በብራዚል አገልግሎት እንዳይሰጥ ለማድረግ መዛታቸውንም መስክ ገልጿል።
ዳኛው በጀመሩት የማህበራዊ ሚዲያዎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የምርመራ መዝገብ መስክን እንደሚያካትቱና የፍርድቤት ትዕዛዝን በመተላለፍ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውም ተዘግቧል።
መስክ ግን “ትዕዛዙን አለመፈጸማችን በብራዚል የምናገኘውን ገቢ ሊያሳጣን፤ ቢሯችን ሊያዘጋን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ከትርፋችን በላይ የምንቆምለት መርህ አለ” ብሏል።
የቀድሞውን ትዊተር በ44 ቢሊየን ዶላር የገዛው መስክ ጉዳዩን ከንግግር ነጻነት ጋር አያይዞ ቢያቀርበውም ብራዚል ግን በሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት ላይ የጀመረችውን ጥረት የሚገዳደርና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እንደመናቅ ቆጥራው የቃላት ልውውጡ ቀጥሏል።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ኤለን መስክን ለማብራሪያ የጠራውም ውጥረቱን ለማርገብ ነው ተብሏል።