የሩፔርት ጠቅላላ የሀብት መጠን ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር ወደ 14.3 ቢሊዮን ዶላር ሲያድግ ከዳንጎቴ ደግሞ 12 ደረጃዎችን ከፍ እንዲል አድርጎታል
ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ዳንጎቴን በመብለጥ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ።
ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ጆናታን ሩፔርት ናይጀሪያውን ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴን በመብለጥ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም መሆኑን የብሉምበርግ ቢሊየነርስ ኢንዴክ መረጃ ያመለክታል።
ሩፔርት ካርቴር እና ሞንትብላንክ የመሳሰሉ ብራንዶች ያሉትን እና በአለም ግዙፍ ከሚባሉት የቅንጦት እቃ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሪችሞንት ባለቤት ነው። የሩፔርት ጠቅላላ የሀብት መጠን ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር ወደ 14.3 ቢሊዮን ዶላር ሲያድግ ከዓለም 147 ደረጃ እና ከዳንጎቴ ደግሞ 12 ደረጃዎችን ከፍ እንዲል አድርጎታል።
ብሉምበርግ እንደዘገበው ከሆነ የናይጄሪያዊው ሀብት በ1.7 ቢሊዮን ዶላር ቀንሶ አጠቃላይ ሀብቱ 13.4 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። የዳንጎቴ ሀብት መጠን መቀነስ አብዛኞቹ ኩባንያዎቹ ያሉባትን የናይጀሪያን የኢኮኖሚ ፈተና የሚያሳይ ነው።
ፕሬዝደንት ቦላ ቲንቡ ባለፈው አመት ስልጣን ከያዙ ወዲህ አሁን የሀገሪቱ የኑሮ ውድነት ወደ 30 በመቶ ከፍ እንዲል ምክንያት የሆነውን የነዳጅ ድጎማ ማንሳትን ጨምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች አድርገዋል። ፕሬዝደንቱ የኤኮኖሚ ማሻሻያዎቹ የመንግስትን ወጭ ለመቀነስ እና የረጅም ጊዜ እድገት ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው ይላሉ።
የናይጄሪያ መገበያያ ገንዘብ ናይራ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ አብዛኛው ሀብታቸው ከሀገሪቱ ገንዘብ ጋር ለተያያዘባቸው ዳንጎቴን ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። የ66 አመቱ ነጋዴ አብዛኛውን ሀብታቸውን የሚያገኙት ከሲሚንቶ እና ከስኳር ፋብሪካዎች ሲሆን ባለፈው አመት በናይጀሪያዋ የኢኮኖሚ ከተማ ሌጎስ የነዳጅ ማጣሪያ ከፍተዋል።
ዳንጎቴ ግሩፕ የተባለው የንግድ ድርጅታቸው በነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያው በፈጠረው የምርት መዘግየት እና በአቅርቦት መዛባት ምክንያት በርካታ ችግሮች አጋጥሞታል። ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ብትሆንም፣ ዳንጎቴ ባለፈው ጥር ወር በፎርብስ መጽሄት ለተከታታይ 13ኛ ጊዜ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሀብታም ተብለው ነበር።
ነገርግን ብሉምበርግ በቅርቡ ያወጣው መረጃ ዳንጎቴ በአፍሪካ ሁለተኛ በአለም ደግሞ 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሩፔርት አጠቃላይ ሀብት የጨመረው የቅንጦት እቃዎች ዘርፍ ከፍተኛ አፈጻጸም በማሳየቱ ነው።
ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ቢሊየነር ኒኪ ኦፐንሂመር በ13.3 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሀብት በአፍሪካ ሶስተኛ ሲሆን ግብጻዊው ባለሀብት ናሴፍ ሳዊሪስ ደግሞ በ9.48 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ሆኗል።
ብሉምበርግ እንደፎርብስ ሁሉ የአለም ሀብታም ሰዎች ባላቸው አጠቃላይ ሀብት ላይ ሊኖር የሚችለውን እለታዊ ለውጥ ይከታተላል።