ኢለን መስክ ለዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ 45 ሚሊዮን ዶላር ያዋጣል መባላቸውን አጣጣሉ
የዓለማችን ባለጸጋ ኢለን መስክ በየወሩ 45 ሚሊዮን ዶላር ለማዋጣት ቃል አልገባሁም ብለዋል
የቴስላ ኩባንያ መስራች እና ባለቤት የሆኑት ኢለን መስክ በይፋ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ እንደሆኑ ይነገራል
ኢለን መስክ ለዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ 45 ሚሊዮን ዶላር ያዋጣል መባላቸውን አጣጣሉ፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት የአለማችን ቁጥር ሶስት ቢሊየነር ኤለን መስክ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በየወሩ 45 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ማቀዱን የሚያትቱ ዘገባዎች በስፋት ተሰራጭተዋል።
ወልስትሪት ጆርናል ምንጭቹን ጠቅሶ በወቅቱ እንዳስነበበው ቢሊየነሩ ድጋፉን የሚሰጠው “ፖለቲካል አክሽን ኮሚቴ” (ፒኤሲ) ለተሰኘ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚውል ገንዘብን ለሚሰበስብ ተቋም ነው ብሎ ነበር።
መስክ ለፒኤሲ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ብሉምበርግ ባለፈው ሳምንት ቢዘግብም የቴስላና ስፔስኤክስ ስራ አስፈጻሚው "እኔ ለማንኛውም እጩ እንዳልሰጠሁ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ" ሲል አስተባብሏል።
መስክ ለሮይተርስ እንዳለው እኔ ለየትኛውም ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ እሰጣለሁ አላልኩም ሲሉ ተናግሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ግን የኤክስ (ትዊተር) ባለቤቱ ኤለን መስክ በይፋ ለሪፐብሊካኑ ተወካይ ድጋፍ መስጠቱ አይዘነጋም።
የመስክን ድጋፍ አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለጸጋውን “ትዕቢተኛ” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፥ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸውም መስክ፥ ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጠ ታክስ ይቀንስልኛል ብሎ ስለሚያምን ነው ይህን ያደረገው ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል።
በሰዎች እጅ የተገደሉ እና የመግደል ሙከራ የተደረገባቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች
ኢለን መስክ እና ዶናልድ ትራምፕ ግንኙነታቸው እያደገ ሄዶ ትራምፕ ጄዲ ቫንስን ተጣማሪያቸው አድርገው እንዲመርጡ መስክ ግፊት እስከማድረግ መድረሳቸውም ተነግሯል።
የፊታችን ህዳር ወር ላይ በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራት ፓርቲ እጩ የነበሩት እና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቀናት በፊት ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው አይዘነጋም፡፡
ይህን ተከትሎ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ ጆ ባይደንን ተክተው የዲሞክራት ፓርቲ እጩ ለመሆን በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሲሆኑ እጩነቱን አሸንፈው በፕሬዝዳንት ምርጫው ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ከቻሉ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት የመሆን እድል አላቸው፡፡