ብራዚል ከአንድ ወር በላይ የዘጋችው ኤክስ በድጋሚ እንዲከፈት ወሰነች
የኤለን መስክ ኩባንያ 5 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ከፍሎና በብራዚል ወኪሉን ለመሾም በመወሰኑ ነው እገዳው የተነሳለት
በብራዚል ከ20 ሚሊየን የሚጠጉ የኤክስ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ተገልጿል
የብራዚል ከፍተኛ ፍርድቤት ዳኛ ከአንድ ወር በላይ በሀገሪቱ ተዘግቶ የቆየው ኤክስ(ትዊተር) በድጋሚ አገልግሎት መስጠት እንዲጀመር ወሰኑ።
ዳኛ አሌክሳንደ ደ ሞሬይስ ውሳኔውን ያሳለፉት ቢሊየነሩ ኤለን መስክ የተላለፈባቸውን ቅጣት በመክፈላቸው ነው ተብሏል።
የቀድሞውን ትዊተር በ44 ቢሊየን ዶላር የገዙት መስክ በብራዚል የተዘጋባቸውን ኤክስ ለማስከፈት የ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ከፍለዋል።
ከዚህም ባሻገር በዳኛው እንዲዘጉ የተጠየቁ የተወሰኑ የብራዚላውያን የኤክስ ገጾችን ለመዝጋትና በብራዚል የኩባንያውን ወኪል ለመሾም መስማማታቸውንም ነው ዳኛ ሞሬይስ የተናገሩት።
ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ከኤለን መስክ ጋር ንትርክ ውስጥ የከረሙት ዳኛ አሌክሳንደ ደ ሞሬይስ በመላ ሀገሪቱ ከአንድ ወር በላይ ተዘግቶ የቆየው ኤክስ በ24 ስአት ውስጥ እንዲከፈት አዘዋል።
ኤክስ በብራዚል ዳግም መመለሱን ይፋ ባደረገበት ጽሁፍ “በአስር ሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ብራዚላውያን ተደራሽ መሆን ትልቁ ግባችን ነው፤ የየሀገራቱን ህግ አክብረን ለንግግር ነጻነት መከበር መታገላችን እንቀጥላለን” ብሏል።
በብራዚል ከ24 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚ ያለው ኤክስ በብራዚል ከፍተኛ ፍርድቤት የተላለፈበትን ውሳኔ አላከብርም በሚል በሀገሪቱ የሚገኙ ሰራተኞቹን አባሯ ቢሮውን እስከመዝጋት ደርሶ ነበር።
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ኤክስ የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጫ ሆኗል በሚል የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚለቁ ሰዎች አካውንቶች እንዲዘጉ ብትጠይቅም መስክ “የንግግር ነጻነት ጠባቂ ነኝ” በሚል አሻፈረኝ ማለቱም ይታወሳል።
ብራዚል ማንኛውም የውጭ ኩባንያ በሀገር ውስጥ ከፍርድ ቤት የሚተላለፉ ትዕዛዞችን የሚቀበል ህጋዊ ወኪል ሊኖረው እንደሚገባ ደንግጋለች።
የተዛባ መረጃ የሚያስራጩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አካውንትን እንዲዘጋ ተደጋጋሚ ጥሪ የቀረበለት ኤክስም ራቼል ኮንሴሶን በሚያዚያ ወር ህጋዊ ወኪሉ ቢያደርግም ከአራት ወራት በኋላ ከሃላፊነታቸው ለቀዋል።
የከፍተኛ ፍርቤቱ ዳኛ ኮንሴሶን በቁጥጥር ስር ሊያውል እንደሚችል ሲያስጠነቁ መቆየታቸውና የኤክስ የባንክ ሂሳቦች እንዲታገዱ ማድረጋቸውም አይዘነጋም።
ኤክስ ከብራዚል ደንበኞቹ በማስታወቂያ ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ ታሳቢ በማድረግ ኤለን መስክ “አምባገነን” በማለት ሲቃወማቸው የነበሩትን ዳኛ ውሳኔ ለማክበር መገደዱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ብራዚል ኤክስን በማገድ የመጀመሪያዋ ሀገር አይደለችም፤ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራን፣ ማይናማር፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ቬንዙዌላ እና ቱርክሚኒስታን የኤለን መስኩ ኤክስ በሀገራቸው እንዳይሰራ አግደዋል።
ግብጽ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ብጥብጥ በተከሰተ ወቅት ለአጭር ጊዜ ኤክስን ማገዳቸውም ይታወሳል።