የአሜሪካ ሚስጥራዊ የደህንነት መስርያ ቤት በኢለን መስክ ላይ ምርመራ ሊያደርግ እንደሚችል አስታወቀ
መስክ “በትራምፕ ላይ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ሲደረግ በባይደን እና ሃሪስ ላይ ምንም አይነት ሙከራ አለመደረጉ ያስገርማል” ብሏል
ነጩ ቤት መንግስት መሰል ለአመጻ የሚያንሳሱ ንግግሮች ለቀልድ ቢሆንም እንኳን መባል የለባቸውም ብሏል
የአለማችን ቁጥር አንድ ሀብታም ኢለን መስክ ከጆ ባይደን አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ ያስገባውን ድርጊት ፈጽሟል፡፡
እሁድ እለት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የግድያ ሙከራ መደረጉን ተከትሎ መስክ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ያሰፈረው ጽሁፍ ነው በደህንነት ተቋማት ሳይቀር ጥርስ ያስነከሰበት፡፡
“ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትላቸውን ካማላ ሃሪስን ለመግደል የሚሞክር ማንም ሰው የለም” የሚል ግርምት እና ጥያቄ አዘል ሀሳብ በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር፡፡
መስክ ጹሁፉን በግል ገጹ ላይ ካሰፈረ በኋላ የገጠመውን ከፍተኛ ተቃውሞ እና ትችት ተከትሎ በፍጥነት ጽሁፉን ከገጹ ላይ አጥፍቶታል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ወዳጅ እና ደጋፊ እንደሆነ የሚነገርለት መስክ ትራምፕ ካሸነፉ የመንግስት ተቋማትን አሰራር የሚቆጣጠር ኮሚሽን ሀላፊ አድርገው እንደሚሾሙት ቃል ገብተውለታል፡፡
ነጩ ቤት መንግስት ጹሁፉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “ሀላፊነት የጎደለው ትርክት” ሲል ገልጾታል፡፡
ከዚህ ባለፈም እንደዚህ አይነት ሀሳቦች በአሜሪካ እንደ አዲስ እያበበ የሚገኘውን ፖለቲካዊ አመጽ የሚበረታታ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደትን የሚያቀጭጭ ነው ብሏል።
የአሜሪካ ሚስጥራዊ የደህንነት መስርያቤት (ሲክሪት ሰርቪስ) ቢሊየነሩ የለጠፈውን ጽሁፍ እንደተመለከተው እና መሰል ሀሳቦች በፕሬዝዳንት እና በክፍተኛ አመራሮች ላይ ከሚፈጸሙ ዛቻዎች ተለይተው እንደማይታዩ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የደህንነት መስርያ ቤቱ “እንደ አሰራር የጥብቃ ደህንነት አካሄዳችንን ይፋ ባናደርግም ጥብቃ በምናደርግላቸው የመንግስት ሀላፊዎች ላይ የሚቃጣ ወይም አደጋ ይፈጥራል ብለን ያሰብነው ሁኔታ ላይ በሙሉ ምርመራ እናደርጋለን” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ኢለን መስክ የለጠፈውን ጽሁፍ ካጠፋ በኋላ ጽሁፉን የለጠፈው ለቀልድ በሚል መሆኑን እና ሰዎች ባልተገባ መንገድ እንደተረዱት ተናግሯል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ ላይ ከተቃጣው የመጀመርያ የግድያ ሙከራ በኋላ ቢሊየነሩ ኢለን መስክ የጆ ባይደን እና ካማላ ሀሪስን አስተዳደር የሚያጣጥሉ እንዲሁም የትራምፕ ተችዎችን በነገር የሚወጉ ተደጋጋሚ ጽሁፎቹን በኤክስ ገጹ ላይ እንደሚያሰፍር ይታወቃል፡፡