እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የተቃወሙ የምያንማር ፖሊሶች ወደ ህንድ ኮበለሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር አውንግ ሣን ሱ ጪ በምያንማር በተፈጸመው ወታደራዊ ግልበጣ ለቁም እስር መዳረጋቸው ይታወሳል
ሃገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት በበኩሉ ህንድ ለመልካም ጉርብትና ስትል ኮብላዮቹን አሳልፋ እንድትሰጥ በደብዳቤ ጠይቋል ተብሏል
ከ37 ቀናት በፊት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የተፈጸመባት ምያንማር ዜጎቿ አሁንም ተቃውሟቸውን ወደ አደባባይ ወጥተው በማሰማት ላይ ናቸው።
ስልጣኑን በመፈንቅለ መንግስት የተቆጣጠረው ወታደራዊው ጁንታ ደግሞ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ፤የፕላስቲክ ጥይት እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመጠቀም ሰልፉን ለመበተን የተለያዩ እርምጃዎችን በመቅውሰድ ላይ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት እስካሁን ድረስ መፈንቅለ መንግስቱን ተቃውመው ወደ አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ለተቃውሞ ወደ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የተቃወሙ የሃገሪቱ ፖሊሶች ወደ ጎረቤት አገር ህንድ መኮብለላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ እስካሁን ድረስ 8 ፖሊሶችን ጨምሮ 30 ሰዎች ወደ ህንድ ኮብልለዋል።
በዚህ የተበሳጨ የሚመስለው የምያንማር ወታደራዊ ጊዜያዊ መንግስት “ህንድ ለመልካም ጉርብትናችን ስትል ኮብላዮቹን አሳልፋ ትስጠን” ሲል በደብዳቤ መጠየቁ ተሰምቷል።
የምያንማር ፖሊሶች ወደ ሃገሯ እንደገቡ የገለጸችው ህንድ በበኩሏ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የሚያስችላትን ውሳኔ ከሃገር ግዛት ሚኒስቴር እየተጠባበቀች መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሌሎች ተጨማሪ የምያንማር ፖሊሶች እና ሌሎች ዜጎች ወደ ህንድ ለመግባት በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
55 ሚሊዮን ገደማ የህዝብ ብዛት እንዳላት የሚነገርላት የቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ምያንማር በደቡብ ምስራቅ እስያ የምትገኝ ሲሆን ከ100 በላይ ብሄር ላላቸው ዜጎች መኖሪያ ናት።
በአገሪቱ ተደረገ በተባለ ምርጫ አሸንፈው ስልጣን ላይ የነበሩት የምያንማር ግዛት አማካሪ (ጠቅላይ ሚኒስትር) አውንግ ሣን ሱ ጪ እንደ ጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር የካቲት 1 ቀን 2021 የአገሪቱ ወታደር ስልጣናቸውን በመፈንቅለ መንግስት ቀምቶ የቁም እስረኛ አድርጓቸዋል።
ድርጊቱን በርካታ የዓለማችን አገራት እየኮነኑት እና እያወገዙት ቢሆንም ቻይናን ጨምሮ ሌሎች አገራት ግን ለድርጊቱ ትኩረት ነፍገውታል።