የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ 300 ሚሊየን ሰዎችን ለረሃብ አጋልጧል - የኮፕ28 ፕሬዝዳንት
በድርቅና ጎርፍ አደጋዎች ምክንያት የተፈናቀሉ አፍሪካውያን ቁጥርም በሶስት እጥፍ መጨመሩን ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ተናግረዋል
የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ መካሄዱን ቀጥሏል
አፍሪካ በአለም የበካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከ3 በመቶ አይበልጥም።
ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛዋ ገፈት ቀማሽ አህጉር ሆናለች።
በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር፥ የአህጉሪቱ 1/5ኛ ህዝብ እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ባሉ አደጋዎች ለረሃብ መጋለጡን አብራርተዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም በሶስት እጥፍ ማደጉን ነው ያነሱት።
የአፍሪካን የጠቅላላ ምርት ወይም ጂዲፒ እድገት በየአመቱ በአማካይ የ5 በመቶ ቅናሽ እያሳየ መምጣቱንም በማከል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ቢሆንም ለሌላው አለም አርአያ የሚሆን ተግባርም አላት ነው ያሉት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃበር።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ለበርካቶችም የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
ኬንያ በ2030 ሁሉንም የሀይል ምንጯን የታዳሽ ሃይል ለማድረግ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትንም አድንቀዋል።
ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ከጸሃይ ሃይል የሚያገኙት ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት አመታት በስድስት እጥፍ ማደጉም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመቀነስ እየሄደችበት ያለውን ርቀት ያሳያል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ግማሽ ህዝብ እስካሁን የኤሌክትሪክ ተደራሽ አለመሆኑን በመጥቀስም የሃይል ክፍተቱን በታዳሽ አማራጮች ለመሙላት የፋይናንስ አቅርቦቱ ሊያድግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ለመቀነስ 250 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ቢባልም አህጉሪቱ ያገኘችው ድጋፍ 12 በመቶ ብቻ ነው።
ሀገራት በተለይ ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትሉት የሚገቡትን ቃል ሊፈጽሙ ይገባል ያሉት ዶክተር ሱልጣን አልጀበር፥ በህዳር ወር በዱባይ በሚካሄደው የኮፕ28 ጉባኤ የፋይናንስ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው አብራርተዋል።
ሀገራቸው አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ በታዳሽ ሃይል ልማት የጀመረቻቸውን ሰፋፊ ፕሮጀክሮች አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።