ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኬንያው የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ ጠንካራ ትችት አቀረቡ
በጉባኤው ከመፍትሄ ይልቅ ሀገራት ስራቸውን ማስተዋወቅ ላይ አተኩረዋል ሲሉ ተችተዋል
ሰኞ የጀመረው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “የናይሮቢ መግለጫን” በማጽደቅ ዛሬ ይጠናቀቃል
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “የህዝብ ግንኙነት” ስራ ላያ አተኩሯል ሲሉ ወቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ትክክለኛ መፍትሄ ለማምጣት የተለመደው የጉባኤ አካሄድ አያዋጣም ብለዋል።
“የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋሚያ ማሳደግ” በሚል አርዕስት በተደረገ የጉባኤው ፓናል ላይ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር የተገኙት ፕሬዝዳንቱ “የተለመደ አዙሪት” ያሉትን የመሪዎች “የማስታወቂያ ንግግር” ተችተዋል።
በጉባኤው የሁለተኛ ቀን ውሎ 20 የሚሆኑ የአፍሪካ መሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ መሪዎች የሀገሮቻቸውን እርምጃዎች በማውሳት የወደፊት ስራዎች ላይ ትብብርን አደራ በማለት ንግግር አድርገዋል።
"ወደ ኋላ ተመልሼ ይህን ሰራሁ ብዬ ማውራት አልፈልግም" ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በጉባኤው ላይ ሀገራት የሰሯቸውን ስራዎች ማስተዋወቅ ላይ አተኩረዋል በማለት ተችተዋል።
ወደ ፊት መተንበይ ላይ ማውራቱን እመርጣለሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋሚያ የሚሆን ገንዘብ “ከምዕራባዊያ እጅ መጠበቅን” ነቅፈዋል።
አፍሪካ ለመከላከልና መቋቋም የሚውል “የአየር ንብረት ፋይናንስ” ከምዕራባዊያን እንዲመደብላት እየወተወተች ባለችበት ጊዜ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አማራጭና የተሻለ ነው ያሉትን መፍትሄ ሰንዝረዋል።
ይልቁንም ያሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት፤ የአህጉሪቱን ሀብት ማሰባሰብና ማልማት ላይ በማተኮር ከተመጽዋችነትና ተረጂነት እንውጣ ብለዋል።
“ሰዎች ስለ አህጉሪቱ ሀብት ያወራሉ። የሰው እጅ ከመጠበቅና እጅን ለምጽዋት ከመዘርጋት ለምን የራሳችሁን ሀብት አታሰባስቡም? በአህጉሪቱ ሀብትን የማሰባሰቢያ መንገድ አለ? እንዴት ነው ሀብቱን የምታሰባስቡት? ለአውሮፓ ከኒጀር የሚወጣውን ዩራኒየም ማስተዳደር ትችላላችሁ? አድርጋችሁታልስ? የአህጉሪቱ የማዕድን ሀብትስ? ይህን ሀብት ለአህጉሪቱ ልማት አውለነዋል? ለአየር ንብረት ለውጥስ? እነዚህ ሀብቶች የት ናቸው? ስለ አህጉሪቱ ችግሮችና መፍትሄዎች ሳይሆን ሁሉም ስለ ራሱ ስኬትና ምን እንደሚሰራ ነው እያወራ ያለው” በማለት የተለየ እይታቸውን አጋርተዋል።
“የቤት ስራችሁን ሰርታችሁ ግብና ውጥናችሁን በየዘርፉ ለይታችሁ ንደፉ” ሲሉ ወደ ጉባኤው ጥቆማ የወረወሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ ካልሆነ ግን ጊዜ መፍጀት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከምዕራባዊያን ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ለአፍሪካ የሚሰጠው ገንዘብ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ መጋበዝ ነው ሲሉም እርምጃውን ተችተዋል።
ሙሰኛ መንግስታት እያሉም የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች ጠብ የሚል ውጤት አያመጡም ሲሉም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አክለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ለየት ያለ ሀሳብ ከታዳሚው ጭብጨባ ማግኘቱን አል ዐይን አማርኛ ከጉባኤው አዳራሽ ተበኝቶ ተመልክቷል።