በወለድ ተመን የሚመራነው የተባለው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ምን የተለየ ነገር ይዟል?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች የሚያበድርበት የወለድ ምጣኔ 15 በመቶ እንዲሆን ወስኗል
ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን ይቀጥላሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወለድ ተመን የሚመራ የገንዘብ ፖሊሲን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ባንኩ በአዲሱ ፖሊሲው በማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ማቀዱን ገልጾ ይህም ከባንኩ የመካከለኛ ዘመን ስትራቴጂአዊ ዕቅዶች መካከል ቀዳሚው ነው ብሏል።
ፖሊሲው የገንዘብ እና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የብሄራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ (National Bank Rate) የሚባለው ሲሆን አተገባበሩ የዋጋ ንረት እና የገንዘብ ሁኔታን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከፍ ወይም ዝቅ የሚል እንደሚሆን ተመላክቷል።
ባንኩ ተግባራዊ በሚያደርገው በወለድ ተመን በሚመራ የገንዘብ ፖሊስ ለመጀመርያ ጊዜ 15 በመቶ የሚሆን ሲሆን፤ ምጣኔው ወቅታዊ የዋጋ ንረት ፣ዝቅተኛ የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትና ካለፉት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ የመጣውን የባንክ ብድር ዕድገትን እንዲሆም ሌሎችንም የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያሰገባ መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም የወለድ ምጣኔው ባንኮች እርስ በርስ በሚበዳደሩት ብድር ላይ ከሚከፍሉት ወለድ ጋር የተቀራረበ ነገር ግን ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጧቸው ብድሮች ላይ ከሚያስከፍሉት ከ16-20 በመቶ ከሚደርስ ወለድ ያነሰ ነው ብሏል።
ባንኮች በውድድር ላይ ተመሥርተው ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን ይቀጥላሉ።
በአዲሱ የገንዘብ ማዕቀፍ ተግባራዊ ከሚሆኑ አሰራሮች መካከል ሌላኛው ብሔራዊ ባንኩ በየሁለት ሳምንቱ አከናውነዋለሁ ያለው ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎች ናቸው።
ከባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ ያስችላሉ የተባሉት ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር የሚያደርጋቸው ጨረታዎች፤ በዋናነት በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያላግባብ የተከማቸ የገንዘብ መጠን ካለ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ሥርዓቱ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከባንኮች ጋር የሚገበያይበትን ጨረታ ያካሂዳል።
ሌላው የኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ግብይትን የሚመለከት ሲሆን ይህ አሰራር ሥራ ላይ ሲውል ትርፍ ገንዘብ ያላቸው ባንኮች የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው ባንኮች ማበደር እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ቢሸጋገርም፣ በሽግግሩ ወቅት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቀጥታ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች በጊዜያዊነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን እንደሚቀጥሉ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።