የፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ
አዲሱ የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ ከፋይናንስ ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር እየመከሩ ነው
በውይይቱ ላይ የባንኮች ቁጥር 31 መድረሱና ስምንት ባንኮች ፈቃድ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ተገልጿል
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ዶክተር ይናገር ደሴን የተኩት አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ማሞ ምህረቱ ከፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ ነው ይህ የተገለጸው።
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥው በሁለት አመቱ ጦርነት እና በአለም አቀፉ የኮቪድ ተጽዕኖ ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ነው ወደ ስልጣን የመጡት።
በበርካታ ዘርፎች ምጣኔ ሃብቱን የሚያቃኑ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፉ የሚጠበቁት አቶ ማሞ ዛሬ ከፋይናንስ ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር ምክክር በማድረግ ላይ ናቸው።
በዚሁ ወቅትም የፋይናንስ ዘርፉን ከቁጥጥር ባለፈ በልማትም የሚያካትቱ ስትራቴጂዎች መከተል እንደሚገባ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የባንኩ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታም የፋይናንስ ዘርፉ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።
የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ሀብት፣ ብዛት፣ ተቀማጭ ሒሳብ እና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ነው በማብራሪያቸው ያነሱት።
2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር ከደረሰው የፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ሃብት ውስጥ የባንኮች ድርሻ 2 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር መሆኑንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የባንኮች ቁጥር 31 ደርሷል፤ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ስምንት አዳዲስ ባንኮችን ጨምሮ 71 የሚጠጉ የፋይናንስ ተቋማትም ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቁ ነው ተብሏል።
የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች ቁጥርም ከ12 ሺህ በላይ መድረሱን ነው ብሄራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው።
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥርም ሆነ ቅርንጫፎቻቸው ብዛት እያደገ ቢሄድም የሚሰጡት አገልግሎት ተመሳሳይ የመሆንና የተደራሽነት ችግር እንዳለባቸው ይነሳል።
መንግስት ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ፈቃድ ሰጥቶ ወደ ሀገር ቤት መግባት ሲጀምሩም ፉክክሩ እንዳይከብዳቸው ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሲያነሱ ይደመጣል።
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱም የውጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የሚሰማሩበትን እና የሀገር ቤቶቹም ከጨዋታ ውጭ የማይሆኑበትን ሁኔታ ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት የመስራት ሃላፊነት አለባቸው።