ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት በብር ኖት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ መመሪያ መውጣቱን ገልጿል
ከሰሞኑ ባንኮች የተጻፈበት የብር ኖት እንዳይቀበሉ ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ ተላልፏል በሚል እየተሰራጨ ያለው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡
ባንኩ ይህንን በተመለከተ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከመስከረም 6 እስከ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የብር ኖት ቅያሬ መደረጉን ያስታወሰው ባንኩ ፣ የብር ኖት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚታተም የሕዝብ ሀብት በመሆኑ በጥንቃቄ ተይዞ ሕብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሊገለገልበት እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ከዚህ አንፃር ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት በብር ኖት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲሁም ብዛት ያለው ገንዘብ ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ እንዳይከማች ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር CMD/01/2020 ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም፣ የብር ኖቱ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግል በማስብ በብር ኖቱ ላይ መፃፍ፣ መቅደድና በቀለም ማበላሸት፣ የትኛውንም ዓይነት ጉዳት ማድረስና ምልክቶቹን ያለፈቃድ ማባዛት የተከለከለና በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለማስታወቂያ ሥራ ከተፈለገ ግን ለማባዛት የባንኩን ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን፣ በጣም የተጎዱ የብር ኖቶች ሲያጋጥሙ ከዝውውር ስለሚወጡበት ሁኔታ ዝርዝር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን እና ባንኩ መመሪያውን ወደ አማርኛ በማስተርጎምና በማብራራት ስለብር ኖት አጠቃቀም በየጊዜው ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የሚሠራ መሆኑ ገልጿል፡፡
ይሁንና “የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ” እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡