የምክክር ኮሚሽኑ "በአንዳንድ ወገኖች አጀንዳ" ለመስጠት የሚደረግ እንቅስቃሴ ችግር ሆኖብኛል አለ
ኮሚሽኑ እነዚህ አካላተሰ እነማን ናቸው የሚለውን ከመጥቀስ ተቆጥቧል
ሀገር አቀፍ የምክክር መድረኩ በዓመቱ አጋማሽ ይጀምራል ተብሏል
የካቲት 14፤ 2014 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “በአንዳንድ ወገኖች” አጀንዳ ለመሰጠት የሚደረግ እንቅስቃሴ በጉዞዬ ካጋጠሙኝ ችግሮች አንዱ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ ይህን ያለው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስለሰራቸው ተግባራትና የወደፊት ወጥኖች ላይ በሰጠው መግለጫ ነው።
ኮሚሽኑ ሕጋዊ ሰውነት፣ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሆኖ ሳለ አንዳንድ ወገኖች አጀንዳ ለመሰጠት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስራዬ ካጋጠሙኝ ችግሮ ውስጥ መሆኑን ገልጿል።
እነዚህ ወገኖች እነማን ናቸው የሚለው ጥያቄ የተነሳ ቢሆንም ኮሚሽኑ ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
ኮሚሽኑ ሆኖም ከመንግስት ትብብር እንጂ ጫና አልደረሰብንም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ “ከውስጥም ከውጭም አይጠለፍም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሌሎች ተመሳሳይ ስራ ለመስራት የሞከሩ ሀገራት የገጠማቸው "ክሽፈት" አይገጥመውምም ተብሏል።
ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሀሙድ ድሪሪ ለዚህ ምክንያት ያሏቸውን የጠቀሱ ሲሆን፤ "የተለየ እጣ ፈንታ አለን" ብለዋል።
"ሀገሪቱ ሌላ አማራጭ የሌላት መሆን፣ የእምነት ሀገር መሆኗ እንዲሁም አጀንዳው ከህዝብ የሚፈልቅ መሆኑ የኢትዮጵያን የተለየ ያደርገዋል" ሲሉ ተስፋውን ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ተመሳሳይ ስራ ለመስራት የሞከሩ ሀገራት ላይ ጥናት ማድረጉን የጠቆሙት አምባሳደር ሙሀሙድ፤ አሳታፊና አካታች አለመሆን፣ የውጭና የመንግስት ጣልቃ ገብነትና አጀንዳ ከውጭ መምጣቱ እንዲከሽፉ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ከማህበረሰቡ አጀንዳ ይሰበሰብበታል የተባለው ሀገር አቀፍ ምክክር በ2015 ዓ.ም አጋማሽ ላይ እንደሚጀመር ተነግሯል።
የምክክሩን ሂደቱን “በነፍሰ ጡር ሴት” የመሰሉት ኮሚሽነር መላኩ ገ/ማርያም “ላለመጨንገፍ ተገቢውን ጊዜ መወሰድ አለበት” ብለዋል።
ኮሚሽኑ የሚያነጋግራቸው የማህበረሰብ ተወካዮች እውነተኛ ወኪል መሆናቸው ጥያቄ ተነስቶበታል።
በተለይም ግለሰቦቹ ከመንግስት ጋር ሊኖራቸው የሚችለው ግንኙነት በአካታችነት ላይ እንደ እንቅፋት ተነስቷል። ይህን ለመቅረፍ ናሙና እንዴት ነው የምትወስዱት በሚል ለተነሳ ጥያቄ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መልስ ሰጥተዋል።
“ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር፤ ማንም እንዳይተው ስለሚፈለግ መወከላቸውን [ህብረተሰቡ] ለማወቅ በመንግስት ስርዓት መሄድ ብቻ ሳይሆን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፓርቲዎች፣ ከኃይማኖት መሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች ከሁሉም ላይ ድምጽ ስላለ አማራጭ ድምጾችን መጠቀም እንከተላለን።”
ኮሚሽኑ ከማህበረሰቡ አጀንዳ ከሰበሰበ በኋላ ካበለጸገና ከተቀረጸ በኋላ ዳግም ወደ ህብረተሰቡ በመመለስ ምክክር ያደርጋል ተብሏል።
ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽኑ ድጋፍ፣ ተነሳሽነትና ዝግጁነት መልካም አጋጣሚዎች ፈጥረውልኛል ብሏል::