ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሙስናን የሚዋጋ ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን አሳውቀዋል
ሙስና ከኢትዮጵያ የጸጥታ ሥጋቶች እኩል እንቅፋት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የጸረ ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴው መቋቋም ያሳወቁት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፤ ሙስና ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት ሆኗል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሙስና ዘመቻ እንደሚጀመር ጠቅሰው እንደነበረ ይታወሳል።
"በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የህዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና ህዝቡ እየተማረረ ነው" ብለዋል።
ከሀገሪቱ የጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና እንቅፋት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ለዚህ መንግስት ጠንካራ ስራ መስራትን የግድ ብሎታል ነው ያሉት።
መንግስት መዋቅሩን በመፈተሽና አዳዲስ ሰርዓቶችን በመዘርጋት ለሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርለት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፤ ነገር ግን "ሀገሪቱ ያጋጠሟት ፈተናዎች" በር መክፈታቸውን ተናግረዋል። ፈተናዎቹ የሰሜኑ ጦርነትና ኮሮናን መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ሙሰኞች በየቦታው ተሰግስገውና ትስስር ዘርግተው እየሠሩ መሆናቸውን ጥናት መለየቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መንግሥት በሙስና ላይ "ጠንካራና የማያዳግም ኦፕሬሽን" ማድረግ አለበት ብለዋል።
በዚህም "በአንድ በኩል የመንግሥት ሕጎች፣ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ ይሠራል"፤ በሌላ በኩል ደግሞ "የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ተግባር" እንደሚከወን አስታውቀዋል።
መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሆኖም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሙስና በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን የሚካሄድ በመሆኑ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል።
በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ ያስተባብራል የተባለው ኮሚቴው፤ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን በመለየት ለህግ ያቀርባል።
ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴው፤ ተመስገን ጥሩነህ፣ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ ሰሎሞን ሶቃ፣ አቶ ደበሌ ቃበታ፣ ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ አብዱሃሚድ መሃመድ በአባልነት የያዘ ነው።
ህብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ ለኮሚቴው የሚጠቁምበት አድራሻዎች ይፋ ሆኗል።