የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅሬታ ምን ምላሽ ሰጠ?
ቤተክርስቲያኗ በሀገራዊ ምክክሩ በተሳታፊም ሆነ የአጀንዳ ልየታ ላይ እንድትሳተፍ ጥሪ አለመቅረቡ ቅር እንዳሰኛት ገልጻ ነበር
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በምክክሩ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ተሳትፎ እንዲረጋገጥ እሰራለሁ ብሏል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ሰጥቷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 21 ጀምሮ ሲያካሂደው የቆየውን ምልዓት ጉባኤ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ቤተክርስቲያኗ ለሀገር ሰላምና እርቅ የነበራት ድርሻ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተዘንግቷል የሚል ቅሬታ አቅርባለች።
የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፥ “ኮሚሽኑ በሀገረ መንግስት ምስረታ፣ በሰላም ግንባታ እና አስታራቂነት ትልቅ ድርሻ ላበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተሳትፎ ጥሪ አለማቅረቡ ቅዱስ ሲኖዶሱን ቅር አስኝቶታል” ነው ያሉት በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ቤተክርስቲያኗ በሀገራዊ ምክክሩ የመሳተፍና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር የሚነጋገር ኮሚቴ መሰየሙንም ገልጸዋል።
ለቤተክርስቲያኗ ቅሬታ በመግለጫ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ለሀገራዊ ምክክሩ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩና ቅሬታ ያሳደሩ ጉዳዮችንም ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት በመወያየት ለመፍታት መወሰኑን በአክብሮት የምመለከተው ጉዳይ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ ስራውን እንደጀመረ ከአምስቱ ተባባሪ አካላት አንዱ ከሆነው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን በማውሳትም፥ ጉባኤው በተሳታፊዎች ልየታና በአዲስ አበባ በተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን በመግለጫው ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሌሎች የእምነት ተቋማትን ከሚወክሉ ተወካዮች ጋር በመሆን በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ካሉ ሀገረ ስብከቶቿ የሀይማኖት መሪዎችን በመመደብ የተሳታፊ ልየታው ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓንም ነው ያስታወሰው።
ለዚህ አበርክቶዋ ቤተክርስቲያኗን ያመሰገነው ኮሚሽኑ፥ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጽህፈት ቤት ድረሰ በመገኘት ለመወያየት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በሀገራዊ ምክክሩ የአካታችነት መርህ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር በእኩልነት የሚተገበር መሆኑንም ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።