ታጣቂ ኃይሎችን አግኝቶ ለማናገር ሙከራ መጀመሩን ምክክር ኮሚሽኑ ገለጸ
በነገው እለት በአዲስ አበባ ከተማ 2500 ሰዎች የሚሳተፉበት የምክክሩ ምዕራፍ ይጀምራል
ዋናው ሀገራዊ ምክክር የሚጀመርበት ቀን አለመቆረጡን ኮሚሽኑ ገልጿል
ለዘመናት የተሻገሩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ የህዝብ ጥያቄዎችን በምክክር እፈታለሁ ያለችው ኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቋማ እየንቀሳቀሰች ነው፡፡
ምክክሩ በህዝቦች እና በፖለቲካ ተዋናያን መካከከል ለንትርክ እና ልዩነት መሰረት የሆኑ አብይት አጀንዳዎች ላይ ተመካክሮ መፍትሄን ለማስቀመጥ አለማውን አድርጓል፡፡ ከተቋቋመ ሁለት አመታትን የተሻገረው ኮሚሽኑ በመጣባቸው መንገዶች ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡
ኮሚሽኑ የአካታችነት እና የገለልተኝነት ጥያቄዎች ይቀርቡበታል። በግጭቱ ውስጥ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸው አለመረጋገጡ እና በሀገሪቱ በተለያዩ ማዕዘናት ያሉ ግጭቶች በምክክሩ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚሉ ስጋቶችን በቡዙዎች ዘንድ ተፈጥረዋል።
ይህ ቢሆንም ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ የተሳታፊ ልየታ አጀንዳ የመሳባሰብ እና የስልጠና ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
- በህዳር ወደ ስራ እገባለሁ ያለው የምክክር ኮሚሽን ምን ላይ ደረሰʔ
- “እኔ በአንድ ነገር ገለልተኛ አይደለሁም፤ ያ አንድ ነገር ምንድነው ካልከኝ ኢትዮጵያዊነት” - ፕ/ር መስፍን አርዓያ
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ የሀገሪቷ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ምክክሩ በታሰበው ፍጥነት እንዳይጓዝ ቢያደርጉም ግጭት በሌለባቸው ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ነገርግን አቶ ጥበቡ እንዳሉት ኮሚሽኑ ግጭት ባለባቸው የኦሮሚያ ዞኖች እና የአማራ ክልል እንዲሁም በትግራይ ክልል ቀሪ ስራዎች አሉት።
ከሁለት አመታት ጦርነት መልስ በሚገኝው የትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታዎች በሚፈቅዱበት ጊዜ ወደ ተሳታፊ ልየታ እና ወደ ሌሎች ተግባራት ለመግባት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል አቶ ጥበቡ።
ቃል አየባዩ አሁን ባለው ሁኔታ በትግራይ እና አማራ ክልሎች የተሳታፊ ልየታዎች ገና አልተጀመረም ብለዋል።
ታጣቂዎችን በሀገራዊ ምክክሩ የማሳተፍ ጉዳይ
የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን የሚያነሱ ታጣቂዎች ካልተሳተፉ ምክክሩ ውጤታማ አይሆንም የሚልም ስጋት ይደመጣል።
ተፋላሚ ሀይሎች ወደ ምክክሩ መጥተው ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ለደህንነታቸውም ዋስትና እንደሚሰጥ ቃል የገባው ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ ምን አይነት ውጤታማ ስራዎችን እንደሰራ ቃለ አቀባዩን ጠይቀናቸዋል፡፡
ኮሚሽኑ የማደራደር እና የማስታረቅ ሚና በአዋጅ አልተሰጠውም የሚሉት አቶ ጥበቡ ታደሰ አሳታፊነቱን ለማረጋገጥ ግን ከታጣቂ ሀይሎች ጋር ንግግር ለማድረግ እና ለመገናኝት ሙከራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡
ከየትኞቹ ታጣቂዎች ጋር ተነጋገራችሁ ምላሻቸውስ ምን ነበር? በሚል የጠየቅናቸው ቃል አቀባዩ ለሂደቱ ውጤታማነት በሚል ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡ ጥሪ መደረጉን እና በምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆኑም ሙከራዎች እንደቀጠሉ ናቸው የሚሉት አቶ ጥበቡ ወደፊት ውጤቱን አብረን እናያለን ብለዋል፡፡
የፌደራል መንግስት፣ በአሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና 'ሸኔ' ተብሎ በሽብር ከተፈረጀው ታጣቂ ቡድን እና በአማራ ክልል ደግሞ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብቷል።
አቶ ጥበብ ጥሪ የተደረገላቸውን ታጣቂዎች በስም ባይጠቅሱም ከመንግስት ጋር እየተዋጉ ላሉት ለእነዚህ ታጣቂዎች እንደሚሆን ይገመታል።
በዚህ ምክክር ለመሳተፍ ፍላጎት የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሉ።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች በኮሚሽኑ ላይ እምነት የለንም ያሉ አካላት በምክክሩ እንደማይሳተፉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።ኮሚሽኑ በፓርቲዎቹ አቋም ጉዳይ በይፋ መልስ አልሰጠም።
የአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፍ
ከነገ ግንቦት 21-27 በአዲስ አበባ የሚከናወነው የምክከር ምእራፍ ሶስት ዋና ዋነ ተግበራት የሚያከናወኑበት ነው።
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ በከተማ እና በወረዳ ደረጃ ህበረተሰቡን ይወክላሉ የተባሉ 11 የማህበረሰብ ክፍሎች መለየቱን ገልጿል፡፡
ከነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከከል ደግሞ እድሮች ፣ የመምህራን ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የንግድ ማህበረሰብ ፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ተፈናቃዮች እና ሌሎችም እንደየፈርጃቸው ሀሳብ እንዲያዋጡ ለማድረግ ተሞክሯል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ተሳታፊዎች በምክክርና በዉይይት የአጀንዳ ሀሳብ ይሰጣሉ፣ አጀንዳወችን የጋራ ማድረግ እና ማደራጀት እንዲሁም ለዋናዉ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸዉን መለየት እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚያደርገው የምክክር ምእራፍ መድረክ ከ 2500 በላይ ተወካዮች እንደሚሳተፉበት የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሃ ግብሮችን በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚያከናዉን ነው የተነገረው፡፡
ዋናው ሀገራዊ ምክክር መቼ እንደሚጀመር የተጠየቁት አቶ ጥበቡ ሂደት በመሆኑ የተቆረጠለት ቀን የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በሂደቱ ምክክር እንዲካሄድባቸው የሚቀረጹ አጀንዳዎች እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዲስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ እና ጥልቀትና አግባብነት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው መርሆዎች ተቀምጠውለታል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የአለመግባባት ወይም የሀሳብ ልዩነቶች የሚታይባቸው ጉዳዮች እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ እንደመሆናቸው መጠን በአጀንዳዎቹ ላይ በራሱ አለመግባባቶች ይታያሉ፡፡
ለተወሰነው ሰው አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮች ለሌላው አጀንዳ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ጉዳዮችን አይነኬ ለማድረግ የሚሞክሩ አመለካከቶችም አሉ፡፡
ኮሚሽኑ ነገ በመዲናዋ በሚጀምረው በቀጣይም በክልሎች በሚያከናውናቸው መድረኮች አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ከላይ በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት ለምክክር እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትጥቅ ግጭት እና ሌሎች ልዩነቶች በምክክር እና በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።