ምርጫ ባልተካሄደባቸው ሶስት ክልሎች የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን ቦርዱ አስታወቀ
ምርጫ ባልተካሄደባቸው የሀረሪ፣ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን ቦርዱ አስታወቀ
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ስለተገኘ መስከራም 24 እንደሚመሰረት አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ከተካሄደባቸው ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ውጪ ጷግሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫውን ለማካሄድ ቀን ቀጠሮ አስቀምጦ ነበር።
ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫው ሰኔ 14 ቀን ባልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት ምርጫውን ለማራዘም መስማማቱን ከዚህ በፊት ገልጿል። በዚህም መሰረት ምርጫውን መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ለማካሄድ ቀን መቁረጡን ያሳወቀ ሲሆን በሶስት ክልሎች የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን ቦርዱ አስታውቋል።
የመራጮች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልሎችም ሀረሪ፤ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እንደተጀመረ ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ምርጫ ቦርድ በጸጥታ እና ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዙ በተፈጠሩ ክፍተቶች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ ባልተካሄደባቸው ሌሎች የምርጫ ክልሎች ላይ ቦርዱ እስካሁን ያወጣው መረጃ የለም።
አማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን ምርጫ ያልተካሄደባቸው ተጨማሪ የምርጫ ክልሎች ናቸው።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን የእንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫዎችን እንዳገኘ በቦርዱ መገለጹ ይታወሳል። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብልጽግና ፓርቲ የፊታችን መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም መንግስት እንደሚመሰርት በትናንትናው ዕለት ማሳወቁ አይዘነጋም።