ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልል ፖሊስ ያሰራቸውን እጩዎች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በመሰቃና በማረቆ ቁጥር 2 የምርጫ ክልል የታሰሩ በግል ለመወዳደር የተመዘገቡት ሁለት እጩዎች እንዲፈቱ ለደቡብ ክልል ፖሊስ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል፡፡
ቦርዱ አደረኩት ባለው ማጣራት ሁለቱ የታሰሩት ዕጩዎች ማለትም አቶ ሁሴን አባቴና አስቻለው ቡባ የካቲት 26 በምርጫ ክልል ጽ/ቤት በነበሩበት ወቅት መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የክልሉ ፖሊስ እጩዎቹን ያሰረው ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት ወንጅል መሆኑን መረዳቱንና ቦርዱ እጩዎች ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ምርጫ እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንደማይያዙ የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በመጥቀስ ጽፏል፡፡
ቦርዱ የክልሉ ፖሊስ የታሰሩትን እጩዎች በአስቸኳይ እንዲለቅና ለምርጫ ክልል ጽ/ቤቱና ለምርጫ ቦርድ እንዲያሳውቅ አሳስቧል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተራዘመው ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጧል፡፡ በምርጫው 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክት የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 47ቱ ተወዳዳሪ እጩ አስመዝግበዋል፡፡