ኢሰመኮ በ“ምርጫ 2013” መከበርና መፈጸም ያለባቸውን 6 ነጥቦች ይፋ አደረገ
በምርጫ 2013 ለመወዳደር 49 ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ምልክት ወስደዋል
ኢሰመኮ “ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት” ሰብአዊ መብት በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ጠይቋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ በመጭው “ምርጫ 2013” መተግበርና መፈጸም አለባቸው ያላቸውን “ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ” ይፋ አድርጓል፡፡
ኢሰመኮ እንዳስታወቀው “ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት” የሰብአዊ መብትን ለመጠቅ የሚወስዱት እርምጃ ማሳወቅ፣ለሰብአዊ መብት መከበር መቆም፣ በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ መስራት ፣ውስብስብ የሆነውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የህግ ማሻሻያ ማድረግ፤ የመደራጀትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበርና ከጥላቻ ንግግር መቆጠብ ሊተገብሯቸው የሚገቡ 6 ነጥቦች ናቸው፡፡
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳኒኤል በቀለ በምርጫው የሰብአዊ መብት ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ ባለድረሻ አካላት “ቃል እንዲገቡ በጠየቅናቸው ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃልኪዳን እንዲያሳውቁ እና በአጀንዳው በተቀመጠው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ” ጥሪ አቅርበዋል።
በመጭው ግንቦት እንዲካሄድ ቀን የተቆረጠለት 6ኛው ሀገራዎ ምርጫ በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫ ቦርድ፤ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ የለም በሚል ካራዘመው በኋላ ነው፡፡
በመጭው ግንቦት ወር ለሚካሄደው ምርጫ እስካሁን 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክታቸውን ከብሄረዊ ምርጫ ቦርድ ወስድዋል፡፡ የተወሰኑ የፖለቲከ ፓርቲዎች ገዥውን ብልጽግና ፓርቲ ጨምሮ ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየካቲት 8፣2013ዓ.ም ጀምሮ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚችሉ አስታውቆ ነበር፡፡