በኢትዮጵያዊው ልብ ጠጋኝ ዶ/ር ፈቀደ አግዋር የተጻፈው ማስታወሻ መጽሐፍ ተመረቀ
መጽሐፉ ዶ/ር ፈቀደ ልብ እና ሳንባ ቆመው ባደረጋቸው የቀዶ ጥገና ህክምናዎች ዙሪያ የሚያጠነጥ ነው
በ17 ታሪኮች የተዋቀረው መጽሐፉ፤ ከታካሚዎቹ አንደበት የተሰባሰቡ ታሪኮች ተካተውበታል
ኢትዮጵያዊው ልብ ጠጋኝ ዶ/ር ፈቀደ አግዋር የጻፈው እና "የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ" የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ/ም ተመረቀ።
መጽሐፉ ዶ/ር ፈቀደ ልብ እና ሳንባ ቆመው ባደረጋቸው የቀዶ ጥገና ህክምናዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ገጠመኞቹ ተካተውበታል።
በ17 ታሪኮች የተዋቀረም ነው። ከታካሚዎቹ አንደበት የተሰባሰቡ ታሪኮችም ተካተውበታል።
• በኢትዮጵያ ልብ እና ሳንባ ቆመው የሚሰጠው ቀዶ ህክምና
ስራውን ሌሎች ሊማሩበት፣ ሊነሳሱበት እና ዋቢ አድርገው በግብዓትነት ሊጠቀሙት እንደሚችሉ በማሰብ መጽሐፉን ጻፍኩት ብለዋል ዶ/ር ፈቀደ በምረቃ ስነ ስርዓቱ።
መጽሐፉ የኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ታሪክ የተሰነደበት እንደሆነም ነው የገለጹት። "ከአሁን በኋላ የእኔ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪክም ነው" ብለዋል።
ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ ህክምናውን በነጻ ለመስጠት በእሳቸውና በአጋሮቻቸው የተቋቋመውን 'ሂሊንግ ቫልቭስ ኢትዮጵያ'ን ለመደጎም እንደሚውልም ነው የተናገሩት።
ዶ/ር ፈቀደ ከአሁን ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በግልና በቡድን 326 ቀዶ ጥገናዎችን ማድረጋቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
231 ገጾች ያሉት "የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ" ዛሬ የዘርፉ ሙያተኞች፣ የህክምናው ተጠቃሚዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተመርቋል።