ስዊድን እና ፊንላንድ ወደ ኔቶ እንዳይቀላቀሉ የሚደረግ ጫና ካለ የኔቶ አጋሮች እርምጃ ይወስዳሉ - የኔቶ ዋና ጸሃፊ
ኔቶን ለመቀላቀል ሂደት ላይ ያሉት ስዊድን እና ፊንላንድ በቅርቡ አባል እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል
ሩሲያ እና ቱርክ የሁለቱም ሀገራት ወደ ኔቶ የመቀላቀል ሂደት ይቃወማሉ
ስዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባል ከመሆናቸው በፊት ከሩሲያ ወይም ሌላ ጠላት ጫና የሚደረግባቸው ከሆነ የኔቶ አጋሮች እርምጃ እንደሚወስዱ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ተና
ስቶልተንበርግ ከስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ስዊድን እና ፊንላንድ በማንኛውም አይነት ጫና ውስጥ ቢገቡ አጋሮች እርምጃ አይወስዱም ብሎ ማሰብ አይቻልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ሂደት ላይ ያሉት ስዊድን እና ፊንላንድ በቅርቡ አባል እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 23 ሀገራት አጽድቀዋል። የቀሩት ሰባት ሀገራትም በቅርቡ እንደሚፈርሙ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጅ ሀገራቱ ኔቶን እንዲቀላቀሉ እስካሁን ፊርማቸውን ካላስቀመጡት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነቸው ቱርክ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት ለአንካራ የገቡትን ቃል እስኪጠብቁ ድረስ ቱርክ የስዊድን እና የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄን እንደማትቀበል በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
"ለሀገራችን የተገባው ቃል እስኪፈጸም ድረስ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋማችንን እንጠብቃለን" ሲሉም ኤርዶጋን በአንካራ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የተደመጡት፡፡
"በስዊድን እና ፊንላንድ የገቡት ቃል መከበሩን አለመፈጸሙን በቅርበት እየተከታተልን ነው፣ በእርግጥ የመጨረሻው ውሳኔ የታላቁ ፓርላማችን ይሆናል" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ሩሲያ በየካቲት ወር በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ የኪቭ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የሰጉት ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት በግንቦት ወር ኔቶ ለመቀላቀል ማመልከታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ምንም እንኳን የኖርዲክ ሀገራት በፍጥነት ለመግባት ተስፋ አድረገው የነበረ ቢሆንም ቱርክ አባልነታቸውን በመቃወም ሂደቱን ልታዘገየው ችላለች።
ኤርዶጋን ሁለቱ ሀገራት የኩርድ ታጣቂዎች መሸሸጊያ በመሆናቸው በተለይም ህገ-ወጥ የሆነውን የኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲን (ፒኬኬ) በማጉላት እና “ሽብርተኝነትን” በማስፋፋት ላይ ናቸው የሚል ክስ ማቅረባቸውንም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው።
በተጨማሪም ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ የኒዩክለር ጦሯን ለማንቀሳቀስ እንደምትገደድ ሩሲያ ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡