ጠቅላይ ሚኒስትሯ መልቀቂያ ያስገቡት ፓርቲያቸው በምርጫ መሸነፉን ተከትሎ ነው
የስዊድኗ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ ፡፡
ባለፈው እሁድ በስዊድን የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመሩት አንደርሰን ፓርቲ በምርጫው ተሸንፏል፡፡
ይሄንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር አንደርሰን የግድ መንግስታቸውን አፍርሰው በምርጫው ላሸነፈው ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ስልጣን ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር አንደርሰን ለሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የስዊድን ግራ ዘመመም ፓርቲዎች ከዚህ በፊት የነበረውን ምርጫ አሸንፈፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ማግደሊና አንደርሰንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሾመው የነበረ ሲሆን አሁን በተካሄደው ምርጫ ደግሞ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በጠባብ ልዩነት አሸንፈዋል፡፡
ግራ ዘመም ፓርቲዎች ምርጫውን 173 ለ176 ድምጽ ልዩነት የተሸነፉ ሲሆን የሞደሬት ፓርቲ መሪ የሆኑት ኡልፍ ክሪሰትረሰን አዲስ መንግስት እንደሚመሰርቱ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡
ላለፉት 11 ወራት ስዊድንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት አንደርሰን የኑሮ ውድነት፣ የስደተኞች አያያዝ እና የግድያ ወንጀሎች መበራከት በምርጫው እንዲሸነፉ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የስዊድን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በሀገራቸው አጥፊዎች ረጅም ዓመት የሚቆይ እስር እንዲፈረድባቸው ማድረግ ፣ስደተኞች ለሀገራቸው ደህንነት አደጋ በማይሆኑበት መንገድ እንዲያዙ እና ሌሎችንም ጉዳዮች የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ዋነኛ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡