ቱርክ ፊንላንድና ስዊድን ቃላቸውን ስላልጠበቁ የኔቶ አባልነት ጥያቄያቸውን እንደማትቀበል ገለጸች
የኪቭ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የሰጉት ፊንላንድና ስዊድን በግንቦት ወር ኔቶ ለመቀላቀል ማመልከታቸው የሚታወስ ነው
ኤርዶጋን፤ ውሳኔው የፓርላ ቢሆንም “ሁለቱ ሀገራት አሁንም የኩርድ ታጣቂዎች መሸሸጊያ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት ለአንካራ የገቡትን ቃል እስኪጠብቁ ድረስ ቱርክ የስዊድን እና የፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄን እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡
"ለሀገራችን የተገባው ቃል እስኪፈጸም ድረስ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋማችንን እንጠብቃለን" ሲሉም ኤርዶጋን በአንካራ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር የተደመጡት፡፡
"በስዊድን እና ፊንላንድ የገቡት ቃል መከበሩን አለመፈጸሙን በቅርበት እየተከታተልን ነው፣ በእርግጥ የመጨረሻው ውሳኔ የታላቁ ፓርላማችን ይሆናል" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ሩሲያ በየካቲት ወር በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ የኪቭ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የሰጉት ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት በግንቦት ወር ኔቶ ለመቀላቀል ማመልከታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ምንም እንኳን የኖርዲክ ሀገራት በፍጥነት ለመግባት ተስፋ አድረገው የነበረ ቢሆንም ቱርክ አባልነታቸውን በመቃወም ሂደቱን ልታዘገየው ችላለች።
ኤርዶጋን ሁለቱ ሀገራት የኩርድ ታጣቂዎች መሸሸጊያ በመሆናቸው በተለይም ህገ-ወጥ የሆነውን የኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲን (ፒኬኬ) በማጉላት እና “ሽብርተኝነትን” በማስፋፋት ላይ ናቸው የሚል ክስ ማቅረባቸውንም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው።
ከዚያም በሰኔ ወር በሶስቱ ሀገራት መካከል ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠትን እና መረጃን መጋራትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ያካተተ ስምምነት ተደርሶ ሁለቱ የኖርዲክ ሀገራት ኔቶን ይቀላቀላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር፡፡
እናም አንካራ አሁን ላይ ሀገራቱ የገቡትን ቃል እየፈጸሙ አይደለም እያለች ነው፡፡ በዚህም ሀገራቱ በሚፈልጉት ፍጥነት ኔቶን የመቀላቀላቸው ጉዳይ አጠያያቂ አድርጎታል፡፡
እስካሁን ከ30 የኔቶ አባላት 28ቱ የፊንላንድ እና የስዊድን አባልነት አጽድቀዋል። የተቀሩት ሃንጋሪ እና ቱርክ ብቻ የአባልነት ጥያቄውን ለማጸደቅ ወደ ፓርላማቸው እንደላኩ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ አዲስ አባል ወደ ህብረቱ ለመቀላቀል የ30ውንም ሀገራት ድጋፍ ስለሚያስፈልግ ቱርክ በሁለቱ ሀገራት መግባት ወይም አለመግባት ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራት እሙን ነው፡፡