በቻይና የሩስያ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የዘንድሮው የኔቶ ጉባኤ ምን ጉዳዮችን ይዳስሳል?
የአባል ሀገራቱ መሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በቀጠናዊ እና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለመምከር በዋሽንግተን ተሰብስበዋል
ኔቶ “በጣለትነት” ፈርጆኛል ያለችው ሩስያ የጉባኤውን ውሳኔዎች በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብላለች
አመታዊው የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ጉባኤ በአሜሪካ ዋሽንግተን መካሄድ ጀምሯል።
እስከመጪው ሀሙስ ድረስ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የ32 አባል ሀገራቱ መሪዎች በዋሽንግተን የከተሙ ሲሆን፤ ከቀዛቃዛው አልም ጦርነት ማብቃት በኋላ አለም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት እየተካሄደ ነው የተባለው የዘንድሮው ጉባኤ በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ዙርያ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተነግሯል።
ጀርመን ለዩክሬን ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ እንዲደረገ ያቀረበችው የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄ በትኩረት ይመክርበታል።
ይህ ወታደራዊ ድጋፍ ቢሊየን ዶላሮችን የሚያስወጣ ሲሆን አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ለሀገሪቱ ከሚሰጡት ድጋፍ ተጨማሪ በኔቶ በኩል የሚደረግ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም እስካሁን ለኬቭ ያልተሰጡ የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች እና የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂውን ለማስታጠቅ አባል ሀገራቱ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ነው የተባለው።
ዩክሬን በኔቶ አባልነት ውስጥ ለመታቀፍ ተደጋጋሚ ጥያቄን ብታቀርብም ስብስቡ እስካሁን ሀገሪቷ አባል የምትሆንበት እድል እንዳለ ከመግለጽ ባለፈ ቁርጥ ያለ ቀን አላሳወቅም።
ተሰናባቹ የኔቱ ዋና ጸሀፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ በመጪዎቹ አስር አመታት ዩክሬን የኔቶ አባል እንደማትሆን በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
ኬቭ በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት ያሉት ዋና ጸሀፊው አባል ትሆን ዘንድ በቅድሚያ ሩስያን ማሸነፍ አለባት ነው ያሉት።
በስብሰባው ትኩረት ከሚያገኙ ጉዳዮች መካከል የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት እያደገ መጥቶ ወደ አባል ሀገራቱ የሚስፋፋ ከሆነ የኔቶ የጦር ስትራቴጂስቶች ያዘጋጁቱን የመከላከያ እቅድ መሪዎቹ የሚያደምጡ ይሆናል።
የኔቶ ወታደራዊ ስትራቴጂስቶች አዲስ በማዘጋጀት ላይ በሚገኙት እቅድ በሩስያ አቅርቢያ የሚገኙ አባል ሀገራት ጥቃት ቢደርስባቸው ለሚሰጠው ምላሽ የሚያስፈልጉ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እና ጦር መሳርያዎች ፣
የወታደሮች ቁጥር ፣ መሰረታዊ የህዝብ መስረተ ልማቶችን እና የመከላከያ ዲፖዎችን በምን አይነት መልኩ መከላከል እንደሚቻል በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን መከናወን በጀመረው አመታዊ ጉባኤ ለአባል ሀገራቱ መሪዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሶስት አስርተ አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ ወታደራዊ እቅድ በጀርመን እና በፖላንድ ወታደሮችን ማስፈር የሚያጠቃልል ነው ተብሏል።
ሩስያ በበኩሏ የኔቶ ስብሰባ ውሳኔዎችን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብላለች። የክሪሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ “ኔቶ እና አባል ሀገራቱ ሩስያን በይፋ በጠላትነት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ የሀገራችንንም ስትራቴጂካዊ ውድቀት የሚፈልጉ በመሆናቸው ውሳኔቸውን በቅርበት እና በንቃት እንከታተላለን” ብለዋል።
ጉባኤው ከሩስያ ቀጥሎ ቻይና ላይ ትኩረቱን አድርጓል በደቡብ ቻይና ባህር እና በምስራቅ እስያ የቻይና ተስፋፊነት ያሰጋኛል ያለችው ዋሽንግተን የቻይናን ተጽእኖ ለመቀልበስ ከኔቶ በተጨማሪ ከኢንዶ ፓስፊክ ሀገራትንም በአጋርነት እያሰባሰበች መሆኑ ታውቋል።
ኔቶ እና አራቱ የኢንዶ ፓስፊክ አጋሮቹ ኒውዝላንድ ጃፓን ደቡብ ኮርያ እና አውስትራሊያ ከቻይና ለሚሰነዘር የሳይበር ጥቃት የጋራ ምላሽ ለመሰጠት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምምነቱ ያስቆጣት ቻይና የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ከሚመለከተው ቀጠና በእጅጉ ርቆ የቀዝቃዛው ዘመን ጠብ አጫሪነት ባህሪ እያንጸባረቀ ነው ስትል ከሳለች።