ኔቶ ከሞስኮ ጋር ፊት ለፊት ከመፋለሙ በፊት እቅድ መንደፍ እንዳለበት ገልጿል
የምስራቅ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በሀምሌ ወር በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ በሽህዎች የሚቆጠሩ ሚስጥራዊ ወታደራዊ እቅዶችን ለማጽደቅ ወጥኗል።
እቅዱ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥምረቱ ለሩሲያ ጥቃት እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥ በዝርዝር ያሳያል ተብሏል። እርምጃው ለአስርት ዓታት የቆየውን የኔቶን መሠረታዊ የአቋም ለውጥን እንደሚያሳይ ተነግሯል።
ኔቶ በአፍጋኒስታንና ኢራቅ ትናንሽ ጦርነቶችን በመዋጋቱ እንዲሁም የድህረ-ሶቪየት ሩሲያ ህልውና ስጋት አለመደቀን ለአስርተ ዓመታት መጠነ ሰፊ የመከላከያ እቅዶችን ማዘጋጀት አላስፈለገውም ነበር ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ነገር ግን በፈረንጆቹ ከ1945 ወዲህ የአውሮፓ ደም አፋሳሽ በተባለው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፤ ኔቶ ከሞስኮ ጋር ግጭት ከመፈጠሩ በፊት እቅድ መንደፍ እንዳለበት እያስጠነቀቀ ነው።
ከኔቶ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት አድሚራል ሮብ ባወር "በችግር አያያዝ እና በጋራ መከላከል መሀል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ይህ ነው። [የግጭቱን] የጊዜ ሰሌዳ የምንወስነው እኛ ሳንሆን ጠላታችን ነው" ብለዋል።
"ግጭት በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ስለሚችል መዘጋጀት አለብን" በማለት አክለዋል።
ኔቶ ቀጣናዊ እቅዶቹን በመተንተን አባላት ኃይላቸውን እና ትጥቃቸውን እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ መመሪያ እሰጣለሁ ብሏል።