ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮች በልምምዱ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል
ኔቶ ሩሲያን ለማስጠንቀቅ ያለመ የጦር አውሮፕላኖች ልምምድ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
በጀርመን አስተባባሪነት የሚካሄደው የኔቶ የጦር አውሮፕላኖች ልምምድ ለአንድ ሳምንት ይቆያል ተብሏል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ የአየር ላይ ውጊያ ልምምድ ማድረግ የጀመረው የጦርነት ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ስለገባው መሆኑ ተገልጿል፡፡
"የአየር መከላከል 23" የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የአውሮፓ ሀገራት የውጊያ አውሮፕላኖች የጋራ ልምምድ ከ250 በላይ የጦር አውሮፕላኖች እንደሚሳተፉበት ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በልምምዱ ላይ 25 የኔቶ አባል ሀገራት እየተሳተፉ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮችም እንደሚሳተፉበት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በልምምዱ ላይ ከኔቶ አባል ሀገራት በተጨማሪ የጃፓን እና ስዊድን የጦር አውሮፕላኖች ይሳተፋሉም ተብሏል፡፡
የጦር ልምምዱ በተለይም የሰው አልባ እና የክሩዝ ሚሳኤል ጥቃቶችን ማክሸፍ በሚቻልበት መንገድ እንደሚያተኩር ነው የተገለጸው፡፡
ከዩክሬን ጋር እየተዋጋች ያለችው ሩሲያ በቀጣይ ሌሎች ሀገራትን ልታጠቃ ትችላለች የሚል ስጋት ያለው ኔቶ፥ የአባል ሀገራቱ ስንዝር መሬት ጥቃት እንዳይደርስበት ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በጀርመን የአሜሪካ አምባሳደር ለዩሮ ኒውስ እንዳሉት የኔቶ አባል ሀገራት የጋራ ልምምድ ለሩሲያ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው፡፡
የኔቶ የአየር ላይ ዉጊያ ልምምድ በአውሮፓ የሚደረጉ መደበኛ የበረራ አገልግሎቶችን ሊያስተጓጉል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡