ጡረታ የወጡ የአውሮፓ ሀገራት አየር ሀይል አብራሪዎች ከየትኛውም ሀገር ጋር የመስራት ህጋዊ መብት አላቸው ቢባልም ከቻይና ጋር መስራታቸው ሊቆም እንደሚገባ ተገልጿል
ቻይና ጡረታ የወጡ የኔቶ አየር ሀይል አብራሪዎችን መቅጠሯ ተገለጸ፡፡
በአሜሪካ እና አውሮፓ በጠላትነት እና በተገዳዳሪነት የተፈረጀችው ቻይና ጡረታ የወጡ የኔቶ አየር ሀይል አብራሪዎችን መቅጠሯን እንደ አዲስ ስጋት እንደሚመለከቱት አስታውቀዋል፡፡
ዶቸቪለ የጀርመንን መከላከያ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ቻይና የአውሮፓን ወታደራዊ ሚስጥሮችን ልታገኝ የሚያስችላትን ድርጊት እየፈጸመች ነው ተብሏል፡፡
በርካታ የጀርመን፣ የብሪታንያ እና አሜሪካ የቀድሞ አየር ሀይል አብራሪዎች ከቻይና ጋር የስራ ውል ፈጽመው ወደ ቤጂንግ አምርተዋል ተብሏል፡፡
ይህም ቻይና ከነዚህ አብራሪዎች የአውሮፓን ወይም ኔቶን ወታደራዊ እውቀቶች እና ቴክኒኮችን በቀላሉ እንድታገኝ ያስችላታል የተባለ ሲሆን ድርጊቱ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የቀድሞ የአውሮፓ ሀገራት የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ ከየትኛውም ሀገር ወይም ተቋማት ጋር የመስራት መብት ቢኖራቸውን ከቻይና ጋር መስራታቸው ግን ስጋት መሆኑን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ከቻይና ጋር እየሰሩ ያሉ የቀድሞ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ውላቸውን እንዲያቋርጡ እና በቀጣይ ሌሎች ወደ ቤጂንግ እንዳያመሩ ሊከለከሉ ይገባልም ተብሏል፡፡
የኔቶ አባል ሀገራት በሲንጋፖር በተካሄደው የዓለም የደህንነት ጉባኤ ላይ ከመከሩ በኋላ የቻይና ድርጊት እንዳሳሰባቸው ተገልጿል፡፤
ቻይና በበኩሏ ከውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ጋር መስራቴ አዲስ አይደለም ጡረታ ከወጡ ከቀድሞ የኔቶ ወይም የአውሮፓ ሀገራት አብራሪዎች ጋር ስሰራ ብዙ አመታትን አስቆጥሬያለሁ ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
የቻይና ጦር ከኔቶ እና ከአሜሪካ የጦር አባላት ስልጠናዎችን ማግኘት ከጀመረ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፣ ድርጊቱ ቻይና በምዕራባዊያን በጠላትነት ከመፈረጇም በፊት የነበረ እንደሆነም አክላለች፡፡