የኔቶ አባል ሀገራት ህዝባቸውን ለጦርነት በማዘጋጀት ላይ ናቸው
ዜጎች ለጥቂት ጊዜያት ሊያገለግሉ የሚችሉ መሰረታዊ ግብአቶችን ገዝተው እንዲያከማቹ ታዘዋል
አሜሪካ ዩክሬን ሩስያን ለማጥቃት የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን እንድትጠቀም መፍቀዷን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገራት ዜጎቻቸውን ለጦርነት እንዲዘጋጁ በማሳሳብ ላይ እንደሚገኙ ተነገረ፡፡
የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በአውሮፓ በተፈጠረው የደህንነት ስጋት ኔቶን የተቀላቀሉት የኖርዲክ ሀገራት ኖርዌይ ፣ ስዊድን እና ፊንላንድ ዜጎች ለተወሰኑ ጊዜያት የምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ቁሶችን ገዝተው እንዲያከማቹ አዘዋል፡፡
ሀገራቱ ህዝቦቻቸው ለጦርነት ወይም ለሌላ ያልተጠበቁ ቀውሶች እንዴት እንደሚዘጋጁ የሚመከር የተለያዩ መረጃዎችን አሳትመው ማሰራጨታቸው ነው የተሰማው፡፡
በዩክሬን ግጭት እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ስዊዲን በዚህ ሳምንት “በቀውስ ወይም ጦርነት ውስጥ” የሚል ርዕስ የተሰጣቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶችን አሳትማ አሰራጭታለች፡፡
የስዊድን የሲቪል ድንገተኛ አደጋዎች ጥበቃ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሚካኤል ፍሪሴል በራሪ ወረቀቶቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራርያ፤ “የጸጥታው ሁኔታ አሳሳቢ ነው እናም ሁላችንም የተለያዩ ቀውሶችን እና በመጨረሻም ጦርነትን ለመጋፈጥ እንዲሁም ለመቋቋም ማጠናከር አለብን ሲሉ” ተናግረዋል።
ፊንላንድ “ለአደጋዎች እና ቀውሶች መዘጋጀት” የሚል አዲስ ድረ-ገጽ የከፈተች ሲሆን ኖርዌያኖች በአስከፊ የአየር ጠባይ፣ ጦርነት ወይም ሌሎች አደጋዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ማቆየት የሚስችል ግብአቶችን እንዲያዘጋጁ የሚያሳስብ በራሪ ወረቀት መቀበል መጀመራቸው ተዘግቧል።
በማስጠንቀቂያ በራሪ ወረቀቶቹ ላይ የሀይል አቅርቦት ቢቆራረጥ ምግብ ለማብሰል እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ የሀይል አማራጮች ፣ ምግብ ፣ መሰረታዊ መድሀኒቶች ፣አልባሳት እና ሌሎችም ቁሶች እንዲከማቹ የሚያዝ ሲሆን ሀገራቱ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ከሆነ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ይገልጻል፡፡
የመጠጥ ውሀ ፣ እንቁላል ፣ ድንች ፣ የስጋ ውጤቶች እና በጽሀይ ብርሀን የሚሰሩ የሀይል አማራጮች በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱ መሰረታዊ ግብአቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ከሰሞኑ የጆ ባይደን አስተዳደር ዩክሬን በሩስያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የረጀም ርቀት ሚሳኤሎችን እንድትጠቀም ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ያለውን ውጥረት አባብሶታል፡፡
ውሳኔው ሀላፊነት የጎደለው እና ሶስተኛው የአለም ጦርነትን የሚያስከትል ነው ያሉት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ለዩክሬን የሚሳኤል ጥቃት በኒዩክሌር ጦር መሳርያ ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ለወትሮው አመጻ ፣ ብጥብጥ ፣ ግድያ እና ጦርነት የማያውቃቸው በሰላማዊነታቸው ከሚጠቀሱ ግንባር ቀደም የአለም ሀገራት መካከል የሚገኙት የኖርዲክ ሀገራት ህዝባቸው በስነልቦና እና በሌሎችም መንገዶች ለጦርነት ራሱን እንዲያዘጋጅ በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡