እስራኤል በጥቅምት ወር በፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም አካል መምታቷን ኔታንያሁ ተናገሩ
ኔታንያሁ የተመታው አካል ምን እንደሆነ ግለጽ አላደረጉም
ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤል የጦር ጀቶች በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በሶስት ዙር ጥቃት አድርሰዋል
እስራኤል በጥቅምት ወር በፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም አካል መምታቷን ኔታንያሁ ተናገሩ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ባለፈው ወር በኢራን ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የቴህራንን የኑክሌር ፕሮግራም አካል በመምታት የመከላከል እና ሚሳይል የማምረት አቅሟ እንዲዳከም ማድረጓን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
"ይህ ሚስጥር አይደለም" ብለዋል ኔታንያሁ በፓርላማ ባደርጉት ንግግር።"በጥቃቱ በኑክሌር ፕሮግራሙ ውስጥ የተመታ አካል አለ።"
የተመታው አካል ምን እንደሆነ ያልገጹት ኔታንያሁ የኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ የማምረት እድል ግን አሁንም ዝግ አይደለም ብለዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ኢራን በ200 ገደማ ሚሳይሎች እስራኤልን ከደበደበች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የእስራኤል የጦር ጀቶች በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በሶስት ዙር ጥቃት አድርሰዋል።
እስራኤል ባለፈው ሚያዝያ ወርም በኢራን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝራ ነበር።
ኔታንያሁ በንግግራቸው እስራኤል በምን ላይ ኢላማ እንዳደረገች በተወሰነ መልኩ ዘርዝረዋል።
የሚያዝያው ጥቃት ኔታንያሁ እንዳሉት ኢላማው ውስን እንደነበር እና ቴህራን አካባቢ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ ኤስ-300 ከመሬት ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳይሎችን ባትሪ ከጥቅም ውጭ አድርጓል።
የጥቅምቱ ጥቃት ደግሞ የቀሩትን ሶሰት ባትሪዎች ማውደሙን እና በኢራን የባለስቲክ ሚሳይል እና ለረጅም ርቀት ሚሳይል የሚሆን ጥጥር ነዳጅ የማምረት አቅሟ ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ኔታንያሁ ገልጸዋል።