ፖለቲካ
በትናንትናው ምርጫ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ከፍተኛ ድምጽ መሰጠቱን ቦርዱ አስታወቀ
በመጪው መስከረም መገባደጃ ላይ አዲስ መንግስት የሚመሰረት መሆኑ ይታወቃል
ቦርዱ ምርጫው ወደ 400 አካባቢ መቀመጫዎች ውክልና ባላቸው ቦታዎች ላይ መካሄዱን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ምርጫ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ መሰጠቱን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ምርጫው ወደ 400 አካባቢ መቀመጫዎች ውክልና ባላቸው ቦታዎች ላይ መካሄዱን አስታውቋል፡፡
የምርጫውንና የቆጠራ ሂደቶችን በማስመልከት መግለጫን የሰጡት የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ በምርጫው “50 +1 መቀመጫ እና ከዚያ በላይ የሆነ ከፍተኛ ድምጽ የመስጠት ሂደት ትናንት አከናውነናል” ብለዋል፡፡
ይህ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
በመጪው ጳጉሜ አንድ የሚካሄደው ምርጫ መንግስት ከሚመሰረትበት ጊዜ አንድ ወር በፊት የሚካሄድ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ቦርዱ የጸጥታ ችግር ባጋጠመባቸው ቦታዎች እና በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የተነሳ ችግር በገጠማቸው 20 ገደማ ምርጫ ክልሎች ጳጉሜ 1 ድምጽ እንደሚሰጥ ከአሁን ቀደም ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
በአብዛኞቹ ምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራ ተጠናቀቆ ውጤት መለጠፉን ያስታወቀው ቦርዱ የተቆጠሩ ድምጾች ወደ ምርጫ ክልሎች መምጣት መጀመራቸውን መግለጹም አይዘነጋም፡፡