ፖለቲከኞቹ የተራራቀ አቋምን በማራመድ ይታወቃሉ
የተራራቀ ፖለቲካዊ አቋም እንደሚያራምዱ የሚነገርላቸው ታዋቂ ፖለቲከኞች በግንባር ሊገናኙ ነው
ጉምቱ ፖለቲከኞችን በግንባር የሚያገናኝ የውይይት መድረክ ከነገ በስቲያ ሃሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ ቦሌ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል፡፡
መድረኩ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ተቋም (ISA) እና በኔዘርላንድስ የመልቲፓርቲ ተቋም (NIMD) ትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን ”ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በኢትዮጵያ፡ተስፋ እና ስጋቶች“ ላይ ይመክራል፡፡
በሚያራምዷቸው ፖለቲካዊ አቋሞች ለመታወቅና ብዙዎችንም ከጎናቸው ለማሰለፍ የቻሉ ብሄርተኛ እና በአንድነት ኃይል አቀንቃኝነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ቀዳሚ ፖለቲከኞች በውይይት መድረኩ ይሳተፋሉ መባሉም መድረኩን ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ጌታቸው ረዳ ከህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወኃት)፣ጃዋር መሃመድ ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ልደቱ አያሌው ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመድረኩ በግንባር ተገናኝተው ስለ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር፣ስለ ወቅታዊ ሃገራዊ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም ስለ መጪው ሃገራዊ ምርጫ እንደሚወያዩ አዘጋጁ ተቋም አስታውቋል፡፡
አንዷለም አራጌ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣አብርሃ ደስታ ከአረና ትግራይ (አረና)፣መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እንዲሁም ኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር) እና ሃሰን ሞዓሊን የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑም ተነግሯል፡፡
መሪውን ብልጽግና ፓርቲን ወክሎ በመድረኩ ሊሳተፍ የሚችል አካል ስለመኖሩ ግን የተገለጸ ነገር የለም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ነጻነት ወ/ሚካዔል (ዶ/ር) ለውይይት መነሻ የሚሆንና የውይይት አጀንዳውን የተመለከተ ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ግን ታውቋል፡፡
ስትራቴጂክ ጉዳዮች ተቋም (ISA) በፖለቲካ፣በደህንነት እና ፖሊሲዎች ዙሪያ ምሁራዊ ጥናትና ምርምሮችን የሚያደርግ የኢትዮጵያ መንግስት ተቋም ነው፡፡