ምርጫ ቦርድ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን የሚጠቀሙ ፓርቲዎች እና እጩዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ
ብልጽግና ፓርቲ አብን ላይ ያቀረበውን አቤቱታ የሚያስረግጥ ማስረጃ አለማግኘቱን ተከትሎ አቤቱታውን አለመቀበሉን ቦርዱ አስታውቋል
ቦርዱ እጩዎችን እስከመሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሃገሪቱ የምርጫ ህግ እና የስነ ምግባር አዋጅ በተጻረረ መልኩ “ለአመጽ የሚጋብዝና በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ስጋትን የሚያጭር ቋንቋ”ን የሚጠቀሙ ፓርቲዎች እና እጩዎችን አሳሰበ፡፡
ቦርዱ ፓርቲዎች እና እጩዎች ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮች እና ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል፡፡
ህጉ የማይከበር ከሆነ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ነው ያሳሰበው፡፡
በአማራ ክልል ከተካሄዱት ሰሞነኛ ትእይንተ ህዝቦች ጋር በተያያዘ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎችን እንቅስቃሴዎችን መከታተሉንም ገልጿል፡፡
በክትትሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)“ሰልፎቹን ተከትሎ ባወጣቸው መግለጫዎች ጥላቻ አዘል ንግግሮችን፣ ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ አገላለጾችን የሚጠቀሙ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት ከምርጫ ፉክክር መንፈስ እና ስነምግባር ውጪ የሆኑ እና በህግ የተቀመጡ በምርጫ ወቅት ተቀባይነት የሌላቸው አገላለጾችን (ንግግር)” መጠቀሙንም ነው ያስታወቀው።
ለዚህም በፓርቲው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ሚያዝያ 10፣11 እና 12 ቀን 2013 ዓ.ም የወጡ ተከታታይ መግለጫዎችን በማያሳያነት አስቀምጧል፡፡
በመግለጫዎቹ ሃይል መጠቀምን እና ግጭትን የሚያነሳሳ ንግግር፣ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ክስ እና በተፎካካሪ አካላት ላይ የሚደረግ ጥላቻን ያዘለ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆነ እና ሰብእናን የሚነካ ንግግር መተላለፉንም ጠቁሟል፡፡
መግለጫዎቹ በምርጫ አዋጁ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ስላለው የቋንቋ አጠቃቀምን የሚደነግገው የምርጫ ስነምግባር መመሪያ የሚጥሱ ናቸው ብሏል፡፡
ይህ የተደረገው በምርጫ ዘመቻ መካከል መሆኑ የምርጫውን ሰላማዊነት ከመጉዳቱም ባሻገር ያልሰለጠነ ፉክክርን ያበረታታል በሚል መስጋቱንም ነው የገለጸው።
በመሆኑም አብን ከዚህ አይነት ተግባር እንዲቆጠብ በአጽንኦት በማሳሰብ ተመሳሳይ መልእክቶች ስርጭት የሚቀጥል ከሆነ እጩ አስከመሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ህዝብ ትዕይንቱን በማስመልከት በሌሎች ፓርቲዎች እና እጩዎች የተደረጉ ንግግሮችን እና የተሰጡ መግለጫዎችንመከታተሉን ያስታወቀው ቦርዱ የብልጽግና ፓርቲ እጩ እና ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አብንን በመተለከተ ያሰፈሩት ገለጻ እና ያልተረጋገጠ ክስ ድንጋጌዎች የጣሰ ነው ብሏል።
እጩዎች በመሰል ንግግሮች የምርጫ ሂደቱን ስጋት ላይ መጣል አግባብ አለመሆኑን በመረዳት በግልም ሆነ በፓርቲ ሲንቀሳቀሱ የስነምግባር ደንቦችን ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ በማሳሰብ ተመሳሳይ ጥሰት በሚፈጽሙት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እስከመውሰድ ሊደርስ እንደሚችል አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮች መቀደዳቸውን ከማህበራዊ ሚዲያዎች መረዳቱንም ነው የገለጸው፡፡
ተግባሩ የምርጫ ወንጀል ነው ያለም ሲሆን ፓርቲዎች፣ እጩዎቻቸው፣ አባላቶቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ሂደቱን ከሚያውኩ የስነምግባር ጥሰቶች እና ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዲቆጠቡ አስገንዝቧል፡፡
ሆኖም ቢልቦርድ እና ባነሮች የተቀደዱት አብን በጠራው ትዕይንተ ህዝብ ነው በሚል ህጋዊ እርምጃን እንዲወስድ ከብልጽግና ፓርቲ የቀረበለትን ቅሬታ የሚያስረግጥ ማስረጃ አለማግኘቱን ተከትሎ አቤቱታውን አለመቀበሉን ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡