አብን ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የህዝብ ቆጠራ መካሄድ እንደነበረበት ሲወተውት መቆየቱን አቶ በለጠ ገልጸዋል
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ሲፈጸሙ የነበሩ ግድያዎችን ለማስቆም መንግስት ይህንን ከሚፈጽሙ ኃሎች ራሱን መነጠልና ይህንንም ማረጋገጥ አለበት ብሏል፡፡
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባረጉት ቆይታ እንደገለጹት በሀገሪቱ በተለይም በመተከል፣ወለጋና ሌሎች ቦታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲቆሙ ለማድረግ መንግስት ራሱን ከጥፋት ኃይሎች መነጠልና ይህንንም በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አቶ በለጠ የጥፋት ስራ የሚያከናውኑ ኃይሎችን መደምሰስና የዜጎችን ሰላም ማረጋገጥ እንዳለበት አንስተዋል፡፡ መንግስት ለዚህ ስራ ቁርጠኛ እስካልሆነ ድረስ ችግሮቹ እደሚቀጥሉም ነው አንስተዋል፡፡
የሕገ መንግስት ማሻሻያ
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ግድያዎችና ሌሎች የፖለቲካ ችግሮች ሕገ መንግስት የወለዳቸው መሆናቸውንም አቶ በለጠ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ የሕገ መንግስት ማሻሻያ መደረግ እንደነበረበት ቀድመን ገልጸናል ያሉት ሊቀመንበሩ አሁን ያለው ሥአርት ፖለቲካውን እየሰራ ያለው በዚህ ሕገ መንግስት መሆኑን አንስተው፤ ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ሕገ መንግስት ማሻሻልን ጨምሮ ሌሎች እንዲህ አይነት መሰረታዊ እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ መጠበቅም እንደሌለበት አንስተዋል፡፡
ምርጫውን ለማድረግ ጊዜው አስቻይና ምቹ ባይሆንም አሁን ያለው መንግስት ሕዝባዊ ቅቡልነት የሌለውና ከሕግም አንጻር ጥያቄዎች የሚነሱበት እንደሆነ ሊቀመንበሩ ያነሳሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ሕዝቡ ባልመረጠውና ይሁንታውን ባልሰጠው ሥርዓት ውስጥ በግዞት እንዳለ ያነሱት አቶ በለጠ ምርጫ ይሁንታ ያላገኘ ሥርዓት እንዲወድቅና ሕዝቡ ይሁንታ በሰጠው ስርዓት ውስጥ እንዲተዳደር ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
አብን ለዚህ ምርጫ ፖሊሲዎችን ማዘጋጀቱን የገለጹት የንቅናቄው ሊቀመንበር ጠንካራ ዕጩዎችን በማዘጋጀት፣ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት በኩል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ፣ አዲስ አበባ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪ፣ ኦሮሚያ፣ደቡብ ክልሎች እንደሚወዳደር የገለጸው አብን ከሞላ ጎደል በመላ ሀገሪቱ እንደሚወዳደር አስታውቋል፡፡
የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ
የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በ10 ዓመት አንድ ጊዜ እንደሚካሄድ በሕገ መንግስቱ ቢደነገግም በኢትዮጵያ ግን ሕዝብም ቤትም ከተቆጠረ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አብን ባለፉት ሁለት ምርጫዎች የአማራን ሕዝብ ሳይንሳዊ የሆነ ቆጠራ እንዳልተደረገለት መግለጹ ይታወሳል፡፡ አጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብም በውል የሚታወቅ ባለመሆኑ መታወቅ እንደነበረበት አብን ገልጿል፡፡በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ከቆጠራው ውጭ ሆኖ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡
አቶ በለጠ ለዚህ ላልተቆጠረ ሕዝብ ማካካሻውም በትክክል ሊተገበር አለመቻሉን ገልጸው በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን የሚደርስ የበጀት ጉድለት እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማጥናታቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ አማራው ብቻ ሳይሆን ሌላውም ሕዝብ ቀጣይ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ሕዝቡ በውል መታወቅ እንደነበረበት አብን ቀድሞ ሲገልጽ መቆየቱን ያነሱት አቶ በለጠ መንግስት ለዚህ ቆጠራ ያለው አጠቃላይ ሕጋዊና ተቋማዊ ቁመና እንዲህ አይነት ትልልቅ ጉዳዮችን ለመፈጸም የሚችልበት እንዳልበረ እንረዳለን ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ የሕዝብና ቤት ቆጠራ አለመደረጉ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸው እስከዛሬ የተጠራቀሙ ችግሮችን መቅረፍ ይቻል ዘንድ አብን ጠንካራ ሆኖ ወደምርጫው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
አቶ በለጠ አሁን ላይ ከኦሮሚያም ሆነ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተሻለ በአማራ ክልል የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰትና የጎብኝ ብዛት ለዚህም ማሳያ እንደሚሆኑም አቶ በለጠ አንስተዋል፡፡ የክልል አስተዳደር አካላት የዜጎችን መብትና ነጻነት ማስከበር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ በለጠ እስካሁን ግን ይህ አለመሆኑን ያነሳሉ፡፡ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንደሳ ግድያ ምክንያት ለግድያ የተዳረጉ ዜጎችን ለማትረፍ መንግስት ቸልተኛ እንደነበር ያነሱት አቶ በለጠ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተዘጋጀውና “መንግስት ያለ አይመስልም “ ነበር የሚለው ሪፖርት ትክክለኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ውይይቶች
ለወራት ያህል የሁለቱ ብሔሮች የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያለመ እንደሆነ አቶ በለጠ አንስተዋል፡፡ ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት በማድረግና ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ደግሞ የተራዘመ ውይይት በማድረግ ለመፍታት መታቀዱን ነው አቶ በለጠ ተናግረዋል፡፡