“የክልሉን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በጅምላ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ነውርና የማይመጥን ፍረጃ ነው”-አማራ ብልጽግና
ኦሮሚያ ብልጽግና የልዩ ኃይል አባላቱ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በሚገኙ ኦሮሞዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው
ለልዩ ኃይል “ያልተገባ ስም” የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙም የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ አሳስቧል
ለአማራ ልዩ ኃይል “ያልተገባ ስም” የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙ የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ አሳሰበ፡፡
ልዩ ሀይሉ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየሰራ ያለውን ስራ ያደነቁት ቢሮ ሃላፊው አቶ ሲሳይ ዳምጤ “ምንም እንኳን የአማራ ስም ቢሰጠው በክልሉ ውስጥ ለሚገኝ ማንኛውም ነዋሪ ሰላም መረጋገጥ እየሰራ ያለ ኢትዮጵያዊ ስብዕናን የተላበሰ ኃይል ነው” ብለዋል፡፡
ለዚህ ሃይል “ያልተገባ ስም” የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙም ነው ቢሮ ኃላፊው ያሳሰቡት፡፡
አቶ ሲሳይ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን እና በአጎራባቹ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተቀሰቀሰውን የፀጥታ ችግር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው በአካባቢው “አንጻራዊ ሰላም” ቢሰፍንም ህብረተሰቡ አሁንም በስጋት ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
ችግሩ በዋናነት “ክልሉን የትርምስና ብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ በማሰብ ኦነግ ሸኔ በተባለ አሸባሪ ቡድን” መቀነባበሩን ተናግረዋል፡፡
“ህይወትያጠፋውን፣ ሀብትና ንብረት ያወደመውን አካል በህግ አግባብ ለመጠየቅ መረጃዎች እየተሰበሰቡ” እንደሚገኙም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲም “የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አንድ ነው” ሲል የጸጥታ ችግሩን በማስመልከት ቀደም ሲል መግለጫ አውጥቶ ለነበረው ኦሮሚያ ብልጽግና ምላሽ የሚመስልን መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው “የኦነግ ሸኔ አባላት በአካባቢው መኖርና መንቀሳቀሳቸውእየታወቀ” የኦሮሚያ ብልጽግና “ሚዛን ያልጠበቀና ችኩልነት የሚጫነው” መግለጫን አውጥቷል ብሏል፡፡
“ተራ ውግንና ያጠላበት ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ አግኝተነዋል”ም ነው ያለው።
“ኦነግ ሸኔና የተልዕኮው ምርኮ የሆኑ ግለሰቦች የፈጠሩት” ነው ባለው ጥቃ ማዘኑን የገለጸም ሲሆን ተጎጂዎችን እንደሚያቋቁም ገልጿል፡፡
“የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንታገል” ሲልም ሁለቱን ህዝቦች ጨምሮ “ዴሞክራሲያዊ” ላላቸው ሁሉም ኃይሎች ጥሪ አቅርቧል።
“ለችግሩ ተደማሪ ችግር ከመሆን ይልቅ መፍትሄው ላይ እንተባበር” ያለም ሲሆን የክልሉን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ “በጅምላ መውቀስና ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ነውርና የማይመጥን ፍረጃ” እንደሆነም አስታውቋል፡፡
“ህዝብን በመያዣነት የሚጠቀም የፖለቲካ ፍልስፍናና መንግስታዊ እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም በአጽንኦት እናሳስባለን”ም ነው ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ያለው።
ይህን ማለቱ በምክንያቶች ገፊነት እንጂ ከብልጽግና ፓርቲ አካልነቱ በመነጠል እንዳልሆነም ገልጿል፡፡
ኦሮሚያ ብልጽግና ኦነግ ሸኔ በሌለበት ስም በመስጠት የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በሚገኙ ኦሮሞዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡