ኔታንያሁ በሄዝቦላ 'ፔጀር' ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ቀጥተኛ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ጽ/ቤታቸው ገለጸ
ኔታንያሁ ከፍተኛ የመከላከያ ኃላፊዎች ፔጀሮችን የማፈንዳት እቅድ መቃወማቸውን እና እሳቸው ግን እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ለሚስትሮች መናገራቸውን ተገልጿል
በሁለት ቀናት ውስጥ በፔጀሮች ላይ በደረሰው ጥቃት በአጠቃላይ 39 ሰዎች ሲሞቱ ከ3400 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላ 'ፔጀር' ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ቀጥተኛ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ጽ/ቤታቸው ገለጸ።
ኔታንያሁ በኢራን በሚደረገው ሄዝቦላ የመገናኛ መሳሪያ 'ፔጀር' ላይ ከፍተኛ ጥቃት እንዲፈጸም የቀረበውን እቅድ ማጽደቃቸው የጽ/ቤታቸው ቃል አቀባይ ኦመር ዶስሪ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው አመት ጥቅምት ጀምሮ በድንበር ላይ ከሄዝቦላ ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርግ የቆየው የእስራኤል ጦር በመጀመሪያ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ ተጠይቆ መልስ አልሰጠም ነበር።
ባለፈው መስከረም ወር በሺዎች የሚቆጠሩ ፔጀሮች በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ እና በሌሎች የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ በተመሳሳይ ሰአት አዲስ መልክት ከገባባቸው በኋላ ፈንድተዋል።
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሄዝቦላ ባለስልጣን ክስቱት ከእስራኤል ጋር እያካሄደ ባለው አንድ አመት ባስቆጠረው ጦርነት ውስጥ ከባድ የሚባል አደጋ ነው ብሏል። በጥቃቱ ጉዳት አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ ተጎጅዎች ውስጥ ብዙዎቹ የአይን ጉዳት፣ የእጅ ጣት መቆረጥ እና የሆድ መቀደድ ማስከተሉን ሮይተርስ እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሁለት ቀናት ውስጥ በፔጀሮች ላይ በደረሰው ጥቃት በአጠቃላይ 39 ሰዎች ሲሞቱ ከ3400 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በካቢኔ ስብሰባ ወቅት ከፍተኛ የመከላከያ ኃላፊዎች ፔጀሮችን የማፈንዳት እቅድ መቃወማቸውን እና እሳቸው ግን እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ለሚስትሮች መናገራቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የሄዝቦላ ታጣቂዎች እስራኤል ያሉበትን ተከታትላ እንዳትደርስባቸው ፔጀሮችን ሲጠቀሙ ነበር። ፔደር መልክት የሚቀበል እና የሚያሳይ ገመድ አልባ የመገናኛ መሳሪያ ነው።
እስራኤል ፔደሮችን ማፈንዳቷን ተከትሎ በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የሄዝቦላ መሪ የነበረውን ሀሰን ነስላሀን ገድላለች።