ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ምን አይነት ፖሊሲ ይከተሉ ይሆን?
እያደገ የሚገኝው የቻይና እና ሩስያ ተጽዕኖ ከትራምፕ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ማተኮር ጋር ሲደመር አሜሪካ በአፍሪካ ጉዳይ ብልጫ ሊወሰድባት እንደሚችል እየተነገረ ነው
ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት እየተወዳደሩ የሚገኙት ራይላ ኦዲንጋ አፍሪካ ከአሜሪካ ውጪ ሌሎች ጠንካራ አጋሮች አሏት ብለዋል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ምን አይነት ፖሊሲ ይከተሉ ይሆን?
ትራምፕ በመጀመርያ የስልጣን ዘመናቸው አፍሪካ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራትን በተመለከተ በሚሰነዝሯቸው አሉታዊ ሀሳቦች በአህጉሪቷ ያላቸው ተጽዕኖ ቀንሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በ2021 ወደ ስልጣን የመጣው የጆ ባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ልዩ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ የሩስያ እና ቻይናን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ተንቀሳቅሷል፡፡
ሆኖም የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ኢምባሲዎች ያጋጠመው የበጀት እና ሰራተኞች እጥረት አስፈላጊውን አላማ ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት አክሽፏል፡፡
ባለፉት አራት አመታት በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ውድቀት ገጥሞታል የሚባለው የአሜሪካ ዲፕሎማሲ በኒጄር የስለላ እና ወታደራዊ ካምፖቿን እንድታጣ እና ከሀገሪቱ ያስወጣቻቸው ወታደሮቿንም ማስፈርያ ሀገር እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት በሳህል ቀጠና ጠንካራ ይዞታ እንዳይኖራት የሆነች ሲሆን በአንጻሩ ሩሲያን ቀዳሚ ወዳጃቸው ያደረጉ ወታደራዊ መንግስታት በርክተዋል፡፡
የህዝብ አስተያየቶችን የሚሰበስበው “ጋሉፕ ፖል” ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ዋሽንግተን በአፍሪካ ዲፕሎማሲ በተቀናቃኞቿ ብልጫ እንደተወሰደባት አመላክቷል፡፡
ለዴሞክራት እና ሪፐብሊካኖች በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ተመድበው ያገለገሉት የቀድሞ የሲአይኤ ተንታኝ ካሜሮን ሀድሰን፤ “አሜሪካ ስትራቴጂያዊ ፍላጎት በምታንጸባርቅባቸው የአፍሪካ ሀገራት ያለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሁኔታዎች መለዋወጥ ፈጣን ቢሆንም ባለፉት አራት አመታት ከዚህ ፍጥነት ጋር የሚጓዝ ፖሊሲ አልነበረንም” ብለዋል፡፡
ዋሽንግተን ለብሔራዊ ደህንነት ወሳኝ ናቸው የምትላቸውን ሰፊ የአፍሪካ ማዕድናትን አቅርቦት በማሳደግ ረገድ ያሳየችው መሻሻል እምብዛም ነው፡፡
በአንጎላ በኩል ወሳኝ ማዕድናትን ወደ ምዕራባውያን ሀገራት ለማሻገር የጀመረችው የባቡር ፕሮጀክትም ለመጠናቀቅ ብዙ አመታትን ይፈልጋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እና በሌሎች መድረኮች ላይ በአፍሪካ ጉዳይ ስለሚከተሉት ፖሊሲ በግልጽ ያሉት ነገር የለም፡፡
ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት እየተወዳደሩ የሚገኙት የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚንስትር ራየላ ኦዲንጋ በትራምፕ መመረጥ ዙርያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “አሜሪካ የአፍሪካ ስትራቴጂዊ አጋር ናት፤ ትራምፕ ከአራት አመት በፊት የነበሩት ሰው ናቸው ብየ አላስብም። ነገር ግን በቀድሞ አቋማቸው የሚቀጥሉ ከሆነ አፍሪካ ከአሜሪካ የተሻሉ ጠንካራ አጋሮች እንዳሏት ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ በሚለው ፖሊሲያቸው ለውጭ ሀገራት ጉዳዮች እምብዛም ባይጨነቁም በአህጉሩ በኢንቨስትመንት ፣ በብድር ፣ በኢኮኖሚ ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም ዘርፎች እየበረታ የመጣው የቤጂንግ እና ሞስኮ ተጽዕኖ አካሄዳቸውን እንዲቀይሩ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በቀድሞ የትራምፕ አስተዳደር ያገለገሉ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት ትራምፕ ከባይደን የተለየ አቀራረብ እና በአህጉሪቷ ተጨባጭ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የአፍሪካ መልዕክተኛ የነበሩት ቲቦር ናጄ የትራምፕ አስተዳደር ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብቶች ላይ አሜሪካ ያላትን አቋም በማለዘብ ከሳህል ሀገራት ወታደራዊ መሪዎች ጋር ለመቀራረብ የፖሊሲ ለውጥ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
የዩክሬን እና መካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት ትራምፕ ለአፍሪካ ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ከዚህ ባለፈም እስካሁን የአፍሪካን ጉዳይ የሚከታተል ቡድን አላዋቀሩም በአንጻሩ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ካማላ ሀሪስ የአፍሪካን ቡድን ያዋቀሩት ምርጫው ከመካሄዱ ቀደም ብለው ነበር፡፡