የኔታንያሁ ጽ/ቤት ከእስራኤል ጎን ያልቆመ ማንኛውንም ሀገር ኢራን እና አጋሮቿን እየደገፈ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል
ኔታንያሁ የማክሮን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ጥሪ "አሳፋሪ ነው" አሉ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን እስራኤል በጋዛው ጦርነት የምትጠቀመው የጦር መሳሪያ አቅርቦት እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ አጣጥለውታል።
ፕሬዝደንት ማክሮን ከፈረንሳይ ኢንተር ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄ የመመለስ ጉዳይን ቅድሚያ የምንሰጠው ነው፤ ለጋዛ ጦርነት የሚደረግ የመሳሪያ አቅርቦት መቆም አለበት" ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዝደንቱ በትናንትናው እለት በፓሪስ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የተኩስ አቁም ጥሪዎች ቢደረጉም የጋዛው ጦርነት መቀጠል እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ አክለውም የእስራኤልን የእግረኛ ጦር ሊባኖስ የማስገባት ውሳኔ ተችተዋል።
ኔታንያሁ "አሳፋሪ ናችሁ"ሲሉ ለማክሮን እና በእስራኤል ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ ላቀረቡት ምዕራባውያን መሪዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
በጽ/ቤታቸው በተለቀቀው የቪዲዮ መልእክት "እስራኤል ብትደገፍም፣ ባትደገፍም ማሸነፏ አይቀርም" ያሉት ኔታንያሁ የመሳሪያ ማዕቀብ ጥሪውን "አሳፋሪ" እንደሆነ ገልጸዋል።
ማክሮን ፈረንሳይ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እያቀረበች አለመሆኑን ተናግረዋል። ማክሮን አክለውም "እየተሰማን አይመስለንም። ስህተት ይመስለኛል"፤ ጦርነቱ ወደ ጥላቻ እያመራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማክሮን በሊባኖስ ያለውን ውጥረት ማርገብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤ "ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ መሆን የለባትም።"
የኔታንያሁ ጽ/ቤት ከእስራኤል ጎን ያልቆመ ማንኛውንም ሀገር ኢራን እና አጋሮቿን እየደገፈ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ማክሮን በ19ኛው የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ወይም ፍራንኮፎን ስብሰባ ላይ አሜሪካ እና ፈረንሳይ በሊባኖስ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ "ኔታንያሁ ስህተት ተሰርተዋል፤ ለእግረኛ ጦር ዘመቻው ኃላፊነቱ ይወስዳሉ" ብለዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የእግረኛ ጦር ዘመቻ የከፈተችው የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን የገደለችበትን ጨምሮ ለሁለት ሳምንታት ተከታታይ የአየር ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ነበር።
እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት እየፈጸመችው ያለው ጥቃት አሁንም ቀጥሏል።