የተመድ የሰላም አስከባሪ ሀይል ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቆ እንዲወጣ ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ጠየቁ
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰላም አስከባሪ ጦሩ በስፍራው መገኝት ምንም ጥቅም የለውም ብለዋል
10 ሺህ የሚጠጉ ከ50 ሀገራት የተውጣጡ ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ የሰፈሩት እስራኤል ሊባኖስን የወረረችበት የ1978ቱ ጦርነትን ማብቃት ተከትሎ ነበር
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሀይል ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቆ እንዲወጣ ጠየቁ፡፡
የጦሩ በስፍራው መገኝት “ጥቅም አልባ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ አካባቢውን ለቆ የማይወጣ ከሆነ ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሀይል እና የሀገሪቱ አስተዳደር ሰላም አስከባሪ ሀይሉ ከስፍራው ለቆ እንዲወጣ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ከተመድ ይሁንታን አግኝቶ አያውቅም፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ሄዝቦላህ ሰላም አስከባሪ ሀይሉን ከለላ አድርጎ እየተዋጋን ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እስራኤል የሰላም አስከባሪ ሀይሉ ሄዝቦላህ ከጦር ነጻ ቀጠናው ውስጥ እንዳይደራጅ እና እንዳይንቀሳቀስ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንዳላደረገ ትከሳለች፡፡
ተመድ በበኩሉ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ሰማያዊውን መስመር አቋርጦ ደቡብ ሊባኖስ ከገባ ባሉት ሳምንታት ውስጥ የእስራኤል ወታደሮች የሰላም አስከባሪ ሀይሉን ካምፖች እና ማዘዣ ጣብያዎች በተደጋጋሚ መምታታቸውን አስታውቋል።
በዚህም የእስራል ጦር በመጠበቂያ ማማዎች ላይ በታንክ በፈጸመው ጥቃት አራት የስሪላንካ እና የኢንዶኔዢያ የሰላም አስከባሪ ጦሩ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰምቷል፡፡
ይህን ተከትሎም ተመድ ድርጊቱን የአለም አቀፍ ህግን የጣሰ በሚል ሲገልጸው እስራኤል በጦሩ ላይ ጥቃት ከማድረስ እንድትቆጠብ ከሰሞኑ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጣ ቆይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ትላንት ለተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት “ጦሩን ከአካባቢው ለማስወጣት ፈቃደኛ አለመሆኖት የአባላቱን እና የእስራኤል ወታደሮችን ህይወት አደጋ ላይ እያጣለ ነው፤ በደረሰው ጉዳት እናዝናለን። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄው ጦሩን ከአካባቢው ማስወጣት ነው” ብለዋል፡፡
እስራኤል በሊባኖስ ከፈጸመችውን ወረራ በኋላ በጦርነቱ ማብቂያ ላይ በ1978 በደቡባዊ ሊባኖስ የሰፈረው የተመድ ሰላም አስከባሪ ሀይል የእስራኤል ጦር ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው ለቆ መውጣቱን ለማረጋጋጥ አላማው ያደረገ ተልዕኮ ይዞ ነበር በስፍራው የተሰማራው፡፡
10 ሺህ የሚደርሱ አባላትን የያዘው ጦር የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ “ብሉ ላይን” የተሰኝ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ከጦር ነጻ ቀጠና ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ባለፈው ወር እስራኤል በሊባኖስ ባስጀመረችው መጠነ ሰፊ ጥቃት የሄዝቦላህን ዋና አዛዥ ሀሰን ናስረላህን እና ሌሎች የቡድኑ አመራሮችን ገድላለች፡፡
በተጨማሪም በምድር እና በአየር እያካሄደች በምትገኝው ውግያ ከ2100 በላይ ንጹሀን ሲገደሉ በሚሊየን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡