ኔታንያሁ ለኢራናውያን ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት ምን አሉ?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤልና ኢራን ወደ ሰላም እንዲመጡ ኢራናውያን “አምባገነን” መሪዎቻቸውን መታገል እንዳለባቸው አሳስበዋል
ኔታንያሁ “የሀገራችን ደህንነት ለማስጠበቅ የማንደርስበት ስፍራ የለም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን ለኢራን ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቪዲዮ በተቀረጸ የሶስት ደቂቃ መልዕክታቸው ኢራናውያን “ቀጠናውን ወደ ጨለማ እየከተተ ነው” ያሉትን የሀገሪቱን አስተዳደር አምርረው እንዲታገሉ ጠይቀዋል።
“እስካሁን ስለ ኢራን መሪዎች ብዙ ብለናል፤ የዛሬው መልዕክቴ ግን ለናንተ ለኢራን ህዝቦች ነው” ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት ኔታንያሁ፥ የኢራን አስተዳደር ሊባኖስና ጋዛን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ በሚካሄዱ ጦርነቶች እየተሳተፈ ቀጠናውን ውጥረት ውስጥ ከቷል ሲሉ ወቅሰዋል።
እስራኤል በየቀኑ የኢራን መንግስት “አሻንጉሊቶችን” እየገደለች መሆኑን በማንሳትም ሀሰን ናስራላህ እና የሃማሱን ሞሀመድ ዴይፍ ለአብነት ጠቅሰዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው ህዝቧችን ለመጠበቅ በመካከለኛው ምስራቅ የማትደርስበት ስፍራ እንደሌለ አብራርተዋል።
የኢራን መንግስት የሀገሪቱ ዜጎች ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን ጭቆና እና በደል የጠቀሱት ኔታንያሁ፥ “አብዛኛው ኢራናዊ የሀገሩ አስተዳደር ለህዝቡ ግድ እንደሌለው ያውቃል” ብለዋል።
“ግድ ቢላቸውማ ለኒዩክሌር እና በውጭ ሀገራት ለሚካሄዱ ጦርነቶች የሚያወጡትን ቢሊየን ዶላር ለትምህርት፣ ጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ ያውሉት ነበር" ሲሉም ያክላሉ።
“የኢራን አምባገነን መሪዎች ለእናንተ የተሻለ መጻኢ አያስቡም፤ እናንተ ግን ታስባለችሁ” በማለትም ኢራናውያን ከአገዛዙ ነጻ ለመውጣት እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አይሁዳውያን እና የፋርስ ህዝቦች ረጅም ታሪክ እንዳላቸው በማውሳትም ኢራን ከአያቶላዎቹ አገዛዙ ነጻ ከወጣች እስራኤልና ኢራን ወደ ሰላም እንደሚመጡ ተናግረዋል።
“የኢራን መንግስት በአምስት አህጉሮች የዘረጋው የሽብር መረብ ሲበጣጠስ ኢራን አይታው የማታውቀውን ማየት ትጀምራለች፤ የአለማቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ትሆናለች፤ ኢራናውያን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም ያወጣሉ፤ ይህ ታዲያ ከማያቆም ድህነት፣ ጭቆና እና ጦርነት አይሻልም ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢራናውያን ባስተላለፉት መልዕክት “ጥቂት አክራሪ ፖለቲከኞች የሚሊየኖችን ህልም እንዲያጨልሙ አትፍቀዱላቸው” ነው ያሉት።
“እስራኤል ከናንተ ጎን መቆሟን ማወቅ ይኖርባችኋል፤ ለጋራ ብልጽግና እና ሰላም አብረን እንሰራለን” በማለትም መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
ኔታንያሁ ለኢራናውያን ዜጎች መልዕክት ያስተላለፉት የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የእግረኛ ጦሩን ለማስገባት ተዘጋጅቷል በተባለበትና ውጥረቱ ባየለበት ወቅት ነው።