በኒውዮርክ ከተማ ከ2 ሚሊዮን የሚልቁ አይጦች እንዳሉ ይገመታል
ያላባራው የኒውዮርክና የአይጦች ጦርነት አዲስ አዛዥ አግኝቷል።
የከተማዋ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ፤ ካትሊን ኮርራዲ የተባሉ ሴት እያደገ ያለውን የአይጦችን ብዛት ለመዋጋት በኒውዮርክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ "አይጥ አዳኝ" ሹመዋል።
"ከዚህ በኋላ ብዙ እኔን እና በጣም ያነሱ አይጦችን ታያላችሁ" ሲሉ ከተማ አቀፍ የአይጥ ቅነሳ ዳይሬክተር የሚል ኃላፊነት የተሰጣቸው አይጥ አዳኝ ተናግረዋል።
የቀድሞ መምህር ኮርራዲ አይጦችን ለመዋጋት አዲስ አይደሉም ተብሏል።
ቀደም ሲልም በከተማው የህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአይጥ ቅነሳ ጥረቶችን እንደመሩም ተነግሯል።
የኒውዮርክ ቁጥር አንድ ጠላት የተባሉ አይጦችን ለማጥፋት ከንቲባ አደምስ፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ተብሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው በኒውዮርክ ከተማ የአይጦች ቁጥር በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍ ብሏል።
አንዳንድ ባለስልጣናት የመንገድ ዳር መመገቢያ ቦታቸው መስፋፋት ለችግሩ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
የከተማዋ የአይጦች ብዛት አይታወቅም ተብሏል።
እ.አ.አ. በ 2014 የተደረገ ጥናት ግን በኒውዮርክ 2 ሚሊዮን አይጦች እንዳሉ ያመላክታል።