ለስደተኞች ቦታ የለንም - የኒውዮርክ ከንቲባ
ዴሞክራቱ የኒውዮርክ ከንቲባ ኢሪክ አዳምስ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በስደተኞች ዙሪያ የያዘውን አቋም ተችተዋል
የስደተኞች ቀውስ ዴሞክራቶችን ከሪፐብሊካኖች እያነታረከ ነው
ዴሞክራቱ የኒውዮርክ ከንቲባ ኢሪክ አዳምስ ለስደተኞች ቦታ የለንም አሉ።
ከንቲባው አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በምትገኘው ኤል ፓሶ ከተማ ያልተለመደ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው ይህን ያሉት።
አዳምስ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በስደተኞች ዙሪያ የያዘውን አቋም በተቹበት ንግግራቸው፥ ስደተኞችን የያዙ አውቶብሶች ወደ ኒውዮርክ መግባት አይችሉም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በደቡባዊ አሜሪካ ያለውን የስደተኞች ቀውስ በተመለከተ አፋጣኝ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ነው ያሳሰቡት።
ሪፐብሊካኖች በሚያስተዳድሯቸው ግዛቶች ስደተኞችን በአውቶብስ በመጫን ወደ ኒውዮርክ እና ሌሎች የዴሞክራት ግዛቶች እየላኩ ነው።
ባለፉት ወራት የቴክሳስ እና ፍሎሪዳ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ስደተኞችን ወደ ኒውዮርክ፣ ቺካጎ እና ዋሽንግተን ዲሲ መላካቸው ይታወሳል።
ይህም የቤት ችግር በስፋት የሚታይባትን ኒውዮርክ ይበልጥ ቀውስ ውስጥ የሚከታት ይሆናል ነው ያሉት ከንቲባው።
ስደተኞቹ ወደ ኒውዮርክ ከገቡ በበጀት እጥረት ውስጥ ያለችውን ከተማ ተጫማሪ 2 ቢሊየን ዶላር ያስወጣታል ሲሉም ነው ኢሪክ አዳምስ የተናገሩት።
ከ40 ሺህ በላይ ስደተኞች ከባለፈው አመት ወዲህ ወደ ኒውዮርክ መግባታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የከተማዋ ከንቲባም የፌደራሉ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ተደጋጋሚ ጥሪ ካደረጉ በኋላ ነው በኤል ፓሶ ጉብኝት ያደረጉት።
በ2021 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ስደተኞች የአሜሪካን ድንበር አቋርጠው ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ መያዛቸውን የሀገሪቱ የድንበር ቁጥጥር መስሪያ ቤት አስታውቋል።