ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሄዝቦላ ላይ "በሙሉ አቅም" ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዛቱ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአሜሪካ እና በአውሮፓ ባለስልጣናት በቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ላይ ጥላውን አጥልቶበታል
እስራኤል ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ እየወሰጀችው ባለው የአየር ጥቃት ሊባኖስ ውስጥ 700 ሰዎች ተገድለዋ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሄዝቦላ ሮኬት መተኮሱን እስከሚያቆም ድረስ "በመሉ አቅም" የአየር ጥቃት እንደሚፈጽሙበት ዝተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአሜሪካ እና በአውሮፓ ባለስልጣናት በቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ላይ ጥላውን አጥልቶበታል።
እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ላይ አዲስ ጥቃት በመክፈት ከፍተኛ የሄዝቦላ አዛዥ የገደለች ሲሆን ሄዝቦላም በደርዘን የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል። በድንበር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን እና ሊባኖሳውያን በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለዋል።
ኔታንያሁ ለተመድ ጠቅላላ ስብሰባ በኒው ዮርክ የደረሱ ሲሆን በእዚያ የሚገኙት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ባለስልጣናት ግጭቱ ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዳያመራ የዲፕሎማቲክ ስራ ለመስራት ለ21 ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም እንደሚቀበሉ ጫና እያሳደሩባቸው ነው።
እስራኤል፣ በኢራን የሚደገፈውን ሄዝቦላ ወታደራዊ አቅም ለማዳከም በሚል ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ እየወሰጀችው ባለው የአየር ጥቃት ሊባኖስ ውስጥ 700 ሰዎች ተገድለዋል። የእስራኤል መሪዎች ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው የጋዛ ጦርነት ጀምሮ ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን እየተናገሩ ነው።
የእስራኤል "ፖሊሲ ግልጽ ነው"ብለዋል ኔታንያሁ።
"ሄዝቦላን በሙሉ አቅማችን ማጥቃታችንን እንቀጥላለን፤ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መመለስን ጨምሮ ሁሉንም ግቦቻችንን ሳናሳካ አናቆምም" ብለዋል።
ቆየት ብለው የኔታንያሁ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል እና የአሜሪካ ባለስልጣናት በተኩስ አቁም እቅዱ ላይ በትናንትናው እለት መወያየታቸውን እና ወደፊትም እንደሚመክሩበት አስታውቋል።
እስራኤል ከፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች በአንዱ የሄዝቦላ የድሮን አዛዥ የሆነው ሞሀመድ ሁሴን ሱሮር በቤሩት ዳርቻ ተገድሏል። እስራኤል ግድያውን ያሳወቀች ሳሆን ሄዝቦላም ቆየት ብሎ አረጋግጧል።
እስራኤል ተጠባባቂ ኃይሏን ከጠራች ከአንድ ቀን በኋላ የእስራኤል ጦር ሀገሪቱ ከሊባኖስ ጋር ወደምትዋሰንበት ሰሜናዊ ድንበሮች ታንክ እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን እያስጠጋ ነው።
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ቦሀቢብ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ "በሁሉም ግንባሮች" አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ ይህ የቀጠለው ግጭት ካልቆመ፣ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ሰላም እና መረጋጋትን አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ቅርቃር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።