በናይጀሪያ በፈንጣጣ መሰል ወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 21 ደርሷል
የዝንጀሮ ፈንጣጣን መከሰት ተከትሎ ናይጀሪያ ዜጎቿ ከጫካ የሚታደኑ ምግቦችን እንዳይመገቡ አገደች፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጀሪያ እየተስፋፋ የመጣውን ፈንጣጣ መሰል ወረርሽኝ ለመከላከል ከጫካ የሚታደኑ ምግቦችን አግዳለች፡፡
በአዲሱ የናይጀሪያ መንግስት ውሳኔ መሰረት ማንኛውም ዜጋ ከጫካ የሚታደኑ ምግቦች እንዳይዘዋወሩ፣ እንዳይሸጡ እና ለምግብነት ሲያውል የተገኘ ግለሰብ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡
በዚህ ሳምንት ስድስት ሰዎች በዚህ ወረርሽኝ የተጠቁ ሲሆን በአጠቃላይ በበሽታው የተጠቁት ዜጎች ቁጥር 21 ሲደርስ አንድ ሰው ደግሞ ህይወቱ ማፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከጫካ ታድነው ለምግብነት የሚውሉ ምግቦች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ሊያሻቅበው ይችላል በሚል ስጋት ነው፡፡
አሁን ላይ በብዙ የዓለማችን ሀገራት በመሰራጨት ላይ ያለው ፈንጣጣ መሰል ወረርሽኝ ከዚህ በፊት በናይጀሪያ ገጠራማ አካባቢዎች ይከሰት እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይህ ወረርሽኝ ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ በ2017 በናይጀሪያ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም ከ2020 በኋላ ግን በሁሉም የሀገሪቱ አካባዎች ላይ ተከስቷል ተብሏል፡፡
ተመራማሪዎች እስካሁን ስለ ቫይረሱ ተጨማሪ ግኝቶችን ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት በመዛመት ላይ መሆኑን በመናገር ላይ ነው፡፡
በሽታው ከሰው ወደ ሰው በሚፈጠር ንኪኪ፣ በትንፋሽ ፣በአይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በሚፈጠር አካላዊ ንኪኪ እንደሚተላለፍ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋ፡፡በቫይረሱ የተጠቁ እንስሳቶች ከሰዎች ጋር ንኪኪ ከፈጠሩ በሽታው የመሰራጨት እድሉ ከፍተኛ እንደሆነም በመነገር ላይ ይገኛል፡፡
ጀርመን፣ አየርላንድ፣ አንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ስፔን፣ፖርቹጋል፣ሆላንድ እና ጣልያን ቫይረሱ በስፋት ከተሰራጨባቸው የአውሮፓ ሀገራት ዋነኞቹ ሲሆኑ ቫይረሱ ከአውሮፓ ሀገራት ውጪ 136 ሰዎችን አጥቅቷል ተብሏል፡፡
ከአፍሪካ ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨባቸው ያሉ ሀገራት መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡