አውሮፓ እና አሜሪካ በፈንጣጣ መሰል ወረርሽኝ ተመቱ
እንግሊዝ፣ ፖርቹጋል፣ ስፔን እና አሜሪካ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ሀገራት ናቸው
በዝንጆሮዎች ላይ በብዛት የሚከሰተው ይህ ወረርሽኝ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ነው ተብሏል
አውሮፓ እና አሜሪካ በፈንጣጣ መሰል ወረርሽኝ ተመቱ፡፡
በአውሮፓ እና አሜሪካ በተለምዶ የዝንጆሮ በሽታ በሚባል የሚታወቀው ፈንጣጣ ወረርሽኝ መመታታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ ወረርሽኝ እስካሁን በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል እና አሜሪካ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በማዕከላዊ እና ምዕራብ አፍሪካ በዝንጆሮዎች ላይ ነበርም ተብሏል፡፡
ይህ በሽታ በአካላዊ ንኪኪ የሚተላለፍ ሲሆን በቫይረሱ የተያዘ ሰው 10 በመቶ የመሞት እድል እንዳለው ተገልጿል፡፡
ወረርሽኙ ከዚህ በፊት ስምንት ጊዜ በዓለማችን የተከሰተ ሲሆን አሁን ደግሞ በፖርቹጋል አምስት ሰዎች፣ ስፔን የበሽታው ምልክት ያሳዩ 23 ሰዎችን እንደለየች ገልጻለች፡፡
በአሜሪካ ደግሞ አንድ ሰው በዚህ ተላላፊ በሽታ የተጠቃ ሰው የተገኘ ሲሆን ከቫይረሱ ተላላፊነት አንጻር ተጨማሪ በሽተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡የዝንጆሮ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ጎርጎሮሲያዊያን ዘመን አቆጣጠር በ1958 በዝንጆሮ ላይ ነበር የተገኘው፡፡
በህ በሽታ አሁን ላይ በእንግሊዝ ዘጠኝ ሰዎች መጠቃታቸው ከታወቀ በኋላ ሰዎቹ እንዴት ሊጠቁ እንደቻሉ ተመራማሪዎች እርግጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡
ተመራማሪዎቹ እስካሁን በዚህ ቫይረስ መጠቃታቸውን ያላወቁ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆን ሰዎች የተለየ ስሜት ከተሰማቸው ወደ ጤና ተቋም እንዲመጡ አሳስበዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ ሰዎች ያለገደብ ወደ ፈለጉት ሀገር እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ለዚህ በሽታ መሰራጨት ዋነ ኛው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም የእንፈግሊዝ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡
የፈንጣጣ ወረርሽኝ በ1980 ዓመት ከዓለም እንደጠፋ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል የተገለጸ ቢሆንም ይሄንን ቫይረስ ማጥፋት የሚያስችለው ክትባት መመረት ቆሟል፡፡
ይሁንና ይህ አዲስ ወረርሽኝ እንደ ኮሮና ቫይረስ እንደ ሀገር የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል የሚያደርስ እርምጃ ለመውሰድ እንደማያደርስ ተገልጿል፡፡