ናይጀሪያ ዜጎች የተጸለየበት በሚል የሚሸጠውን “ተአምራዊ ውሃ” እንዳይጠቀሙ አሳሰበች
የሀገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የታሸገ ውሃ መካን ሴቶችን ያስወልዳል በሚል በሀሰት ለገበያ እየቀረበ ነው ብሏል
የታሸጉት ውሃዎች “ፈዋሽ” ምርቶች ናቸው የሚለው አቅራቢያው ቤተእምነት ግን መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንዳይገባ ጠይቋል
ናይጀሪያ ዜጎቿ “ተአምራዊ” ሃይል አላቸው በሚል ታሽገው የሚሸጡ የውሃ ምርቶችን እንዳይጠቀሙ አሳስባለች።
የሀገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን (ናፍዳክ) በታዋቂው የቴሊቪዥን የወንጌል ሰባኪ ጀርሚያህ ፉፌይን “ተአምራዊ ውሃ” እና “የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ” በሚል ስያሜ የሚቀርቡት የታሸጉ የውሃ ምርቶች ከባለስልጣኑ ፈቃድ አላገኙም ብሏል።
“የተጸለየባቸው” የታሸጉ ውሃዎች መካን ሴቶች እንዲወልዱ የማድረግ ሃይል አላቸው በሚል በሀሰት እየተሸጡ መሆኑንም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።
ምርቶቹን ለገበያ የሚያቀርበው “ክራይስት ሜርሲላንድ ደሊቨረንስ ሚኒስትሪ” በበኩሉ የናይጀሪያን ህግ አክብሮ እንደሚሰራ አስታውቋል።
ህጉ የእምነት ነጻነት ያለምንም ጣልቃገብነት እንዲረጋገጥ የሚደነግግ መሆኑን በመጥቀስም የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣኑን ክስ ጣልቃገብነት ነው ብሎ ተቃውሞታል።
ናፍዳክ በታሸጉት ውሃዎች ላይ ምርመራ የጀመረው ከህብረተሰቡ በደረሰው ቅሬታ መነሻ መሆኑን ባወጣው መግለጫ መጠቆሙን ቢቢሲ ዘግቧል።
የሰባኪ ፉፌን ቤተእምነት ለምርመራው ተባባሪ ለመሆን አለመፍቀዱንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።
በዩቲዩብ በመቶ ሺዎች የሚቆጥሩ ተከታዮች ያሉትና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተደራሽነቱ ሰፊ የሆነው የሰባኪ ፉፌይን ቤተእምነት ግን ከናፍዳክ ጋር በደብዳቤ መልዕክቶችን ሲለዋወጥ መቆየቱን ገልጿል።
ጀርሚያህ ፉፌይን በተአምራትና የፈውስ አገልግሎት በናይጀሪያ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል።
ሰባኪው ምንም እንኳን ቢሊየነር መሆኑን ቢገልጽም ቅንጡ ኑሮው ትችት ያስነሳበታል።
በናይጀሪያ እንደ ፉፌይን ያሉ የፈውስ አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ ሰባኪዎች የተለያዩ “ፈዋሽ” ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ሃብት ያካብታሉ።
ቲቢ ጆሽዋ የተባለው ታዋቂ ሰባኪም ከፍተኛ የመፈወስ አቅም አለው ያለውን “የተጸለየበት ውሃ” ይሸጥ እንደነበር ይታወሳል።
ቢቢሲ በጆሽዋ ላይ በሰራው የምርመራ ዘገባ ሰባኪው ወደ ቤተ እምነቱ የሚመጡ የታመሙ ሰዎች የታዘዘላቸውን መድሃኒት እንዲያቆሙ ያበረታታ እንደነበር አመላክቷል።
በጎን ግን በሚስጢር ያደራጃቸው የመድሃኒት ባለሙያዎች ታማሚዎቹ የታዘዘላቸውን መድሃኒቶች “ፈዋሽ” ናቸው በተባሉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ውስጥ እንዲጨምሯቸው አስደርጎ ታማሚዎቹ እንዲወስዷቸው በማድረግ የቅጥፈት ስራ ይከውን እንደነበር ምርመራው ማሳየቱ የሚታወስ ነው።