የኬንያው ፓስተር 191 ህጻናትን “አስርቦ በመግደል” ተከሰሰ
የቀድሞ የታክሲ ሾፌር ተከታዮቹ ልጆቻቸውን “የሰይጣን ተቋማት” ወዳላቸው ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች እንዳይልኩ ማድረጉ ተጠቅሷል
ፖል ማካንዚና 29 ተባባሪዎቹ የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል
በተሳሳተ አስተምህሮው ከ400 በላይ ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ያደረገው ኬንያዊ ፓስተር ክስ ተመሰረተበት።
“የአለም ፍጻሜ ተቃርቧል፤ በረሃብ ከጸናችሁ ኢየሱስን ታዩታላችሁ” በሚል አስተምህሮው ተከታዮቹን በጫካ ውስጥ ከረሃብ ጋር እንዲታገሉ አድርጓል የተባለው ፖል ማካንዚ በ191 ህጻናት ግድያ ክስ እንደተመሰረተበት ሬውተርስ ዘግቧል።
ማሊንዲ በተባለችው ከተማ ፍርድቤት የቀረበው ማካንዚ እና 29 ተባባሪዎቹ የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቀበሉት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
የቀድሞ ታክሲ ሾፌር “ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ቤተአምልኮ መስርቶ አማኞች ከአለም ፍጻሜ ራሳቸውን ለማዳን በረሃብ ራሳቸውን እንዲቀጡ ማሳሰቡን ክሱ ያስረዳል።
ለረሃብ የማይበገሩ ከሆነ “ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከትና ገነት መግባት ይችላሉ” የሚለውን አስተምህሮውን ያመኑ ተከታዮቹም ሻኮላላ ወደተሰኘ ጫካ መግባታቸውም ነው የተጠቆመው።
ለቀናት ራሳቸውን አግልለው በረሃብ የምጽአት ቀንን ሲጠባበቁም ሞት ቀድሟቸው ከ400 በላይ ሰዎች አስከሬን ከጫካው መውጣቱን የኬንያው ሲቲዝን ቴሌቪዥን ዘገባ ያወሳል።
ማካንዚ ተከታዮቹ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቶችና ቢታመሙ እንኳን ወደ ሆስፒታሎች እንዳይወስዷቸው ማሳሰቡም ተመላክቷል።
ኬንያዊው ፓስተር ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችን “የሰይጣን ተቋማት” ናቸው ሲል የሚገልጻቸው ሲሆን፥ “በረሃብ ገነት የመግባት” አስተምህሮው ከ100 በላይ ህጻናት ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑም ነው በክሱ የተጠቀሰው።
የኬንያ ፖሊስ ፖል ማካንዚ በተሳሳተ አስተምህሮው ምክንያት በሻኮላላ ጫካ ላጠፋው የሰው ልጅ ህይወት ተጠያቂ ነው በሚል በሚያዚያ ወር 2023 በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን፥ ከሽብር ጋር በተገናኙ፣ በጅምላ ግድያ እና ማሰቃየት ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።
ያለፈቃድ ፊልሞችን በማከፋፈል ተከሶም የ12 ወራት እስራት ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ይታወቃል።